በእኔ እምነት ምርጫ ቦርድ ልጓሙን በጥሶ መፈርጠጥ ጀምሯል፡፡ አዎ ምርጫ ቦርድም ሆነ ኢህአዲግ በህግ የበላይነት ሊያምኑና ህግን ሊያከብሩ ብሎም በተሰጣቸው ገደብ መሰረት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዴሞክራሲ፣የህግ የበላይነት ….ወዘተ እያሉ መደስኮሩ ጉንጭ ከማልፋት በተዘለለ ለዜጎች ጠብ የሚልላቸው ነገር አይኖርም፡፡ መንግስታት አንባገነን በሆኑበት አግባብ ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት አስቸጋሪ ነው፡፡ ….በሀገራችንም እየሆነ ያለው ይህ ሀቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ የሀገሪቱ የይስሙላ ህገ መንግስት በአንቀፅ 102 1-2 ስለምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ተቋምነት ቢደነግግም፤ እውነታው ግን ከዚህ ፍፁም ያፈነገጠና ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ለመሆን ቀርቶ የመንግስት ክንፍ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ….እሺ ይኸንንም ይሁን ብለን እንቀበል፤…..ኢህአዲግ ያላከበረውን ህገ-መንግስትና የህግ ማእቀፍ ምርጫ ቦርድ ያከብራል ብለን አንጠብቅ፤…ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ከአንድ ተቋም ነኝ ከሚል መዋቅር የማይጠበቅና እጅግ የወረደ ተግባር ሲሰራ እየተመለከትንበት ያለው ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንና ተቋሙንም ሆነ የተቋሙ አመራሮችን ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያድናቸው ሆኖ አናገኘውም፡፡
ምርጫ ቦርድ እንደተቋም ያስፈፅማቸውና ሊተገብራቸው ዘንድ የሚጠበቁ ተግባራት በህግ ተለይተው ተቀምጠውለት ሳለ በፓርቲዎች አሰራርና የውስጥ ጉዳይ እንደርጎ ዝንብ ጥልቅ እያለ፤በማያገባውና በህግም ሆነ በአሰራር በማይመለከተው ተግባር ውስጥ ህገ-ወጥ ተግባር መፈፀሙ ምናልባትም የሀገራችን ህግ ምን ያህል እንደወረደና የምርጫ ቦርድ ማንአለብኝነት ከኢህአዲግ የጀርባ እጅ ጋር መያያዙንና የህወሀት
/ኢህአዲግና/የምርጫ ቦርድን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታነት ቁልጭ አርጎ የሚያመላክት ነው፡፡
በህግ የበላይነት በሚያምኑ መሪዎችና ህዝቦች መካከል ፤…‹‹ህግ›› ማለት ልጓም ነው፡፡ አንድ ፈረስ በተፈቀደለት አቅጣጫና ፍጥነት በተገቢው ሁኔታ ይሄድ ዘንድ ልጓም ይበጅለታል፡፡ ልጓሙ ህግ ነው፤ ፈረሱ ከልጓም ከወጣ በሰውም ላይ ሆነ በራሱ ላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ …..ልጓሙን ይዞ ፈረሱ ላይ ተግባራዊ የሚያደርገው ደግሞ የጋሪው አሽከርካሪ ነው፡፡ ስለዚህ ባለጋሪው ከፍተኛ ሀላፊነት አለበት ማለት ነው፡፡…..በህዝብም ላይ ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተስማምተው ያወጡት ህገ-መንግስትና የየተቋማቱ ልዩ ልዩ ማስፈፀሚያ ህጎችና የህግ ማእቀፎች በሀገሪቱ ላይ ለሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴና አሰራር ልክ እንደ ልጓሙ ሁሉ ገደብ አድርገውለታል፡፡ …..ከዚህ ልጓም የወጣ ደግሞ፤ …..ህገ-ወጥና የህግን የበላይነት የማያከብር ይባላል፡፡
በሀገራችን ያለው ሁኔታ በልጓም (በህግ) የበላይነት ማመን በወሬ ደረጃ ሆኖ የምናገኘው ኢህአዲግም ሆነ ሌሎች ተቋማት ህግንና አሰራርን በገሀድ ሲጥሱትና ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ሳይኖር ሲቀር ነው፡፡ …..ለነገሩ የሀገሪቱ መንግስት ነኝ ባይ ፓርቲ ህጉን እንዳሻው እየጣሰና እየረገጠ ባለበት ሁኔታ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች ህጉን ቢጥሱ ምን ሊደንቀን ይገባል??? ……. ሰሞኑን እንደተከታተልነው ምርጫ ቦርድ ከተፈቀደለትና ከሚመለከተው ተግባር ውጭ በመውጣት በአንድነት ፓርቲ ላይ የጀመረው የውንብድናና የማንአለብኝነት ተግባር እጅግ አሳፋሪና የወረደ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ …….ምርጫ ቦርድ ‹‹ፅድቁ ቀርቶብኝ፣……›› እንደሚባለው ምንም እንኳ እንደአንድ ገለልተኛ ተቋም ለፓርቲዎች የሚጠበቅበትን ሀላፊነት ከአድሏዊነት በፀዳ መልኩ ማገልገል ቢሳነውም በማያገባው ሁሉ ጥልቅ እያለ የሚፈፅመው የህግ ጥሰትና የአሰራር ዝቅጠት ድርጊቱ ሆን ተብሎና በኢህአዲግ ተልእኮ አስፈፃሚነት የሚሰራ ትወና ለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡ …..ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ላይ የከፈተው የተልእኮ ዘመቻ፤……. መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሊያውቀውና ሊገነዘበው የሚገባ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ እስካሁን በህዝብና በፓርቲዎች ላይ እየፈፀመ ያለው ደባ እንዳለ ሆኖ ልጓሙን የበጠሰው ይህ ተቋም በቀጣይነት ለፓርቲዎች ህግ ላውጣ፤ የፋይናንስ ጉዳያችሁን ላስተዳድር፤የዲሲፕሊንና ሌሎች የፓርቲው እርምጃ በኔ በኩል ይፈፀም፤…ለኢህአዲግ መስገድ በኔ በኩል የሚፈፀም የፓርቲዎች ግዴታ ነው፤የየፓርቲዎችን ፕሬዝዳንት በኢህአዲግ መልማይነት በእኔ አፅዳቂነት ይፈፀም ……. ወዘተ የሚሉ ወራዳና የወረዱ ተግባራትን እንደሚፈፅም አልጠራጠርም፡፡ይህ ተቋም በህዝብ ላይ ለፈፀመው ደባና ንቀት ተጠያቂ የሚሆንበት ቀን እሩቅ አይሆንም፡፡ …..አንድነት ፓርቲና ሌሎች የምርጫ ቦርድ መረን ለቀቅ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ፓርቲዎች ግን የህዝብን አደራ ተሸክመው፤በዚህ ተልካሻና የማይከበር ተቋም ሴራ ከትግሉ መራቅ እንዴሌለባቸው የሚታመን በመሆኑ፤…… በተባበረ ክንድ የምርጫ ቦርድንም ሆነ የኢህአዲግን ውጥን የሚያከሽፍ የትግል ስልት ነድፈው እንደሚንቀሳቀሱ አልጠራጠርም፡፡ ….ምናልባት ፓርቲዎች ባመጡት ጠንቅ ሳይሆን በኢህአዲግና ምርጫ ቦርድ ሴራ ትግሉ ደም የሚያቃባና በመስዋትነት የታጀበ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለዚህ ደም መፋሰስ ተጠያቂዎቹ ኢህአዲግና ምርጫ ቦርድ መሆናቸውን መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሊረዳው የሚገባ ሀቅ ነው፡፡ …….አመሰግናለሁ!!! …….አንብበው ሲጨርሱ ሼር ማድረግዎትን አይርሱ!!! …..ድል የህዝብ ነው!!!
No comments:
Post a Comment