(ዘ-ሐበሻ)
ዶክተር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ መግባታቸውን የዘ-ሐበሻ ታማኝ ምንጮች አረጋገጡ::
የኦነግ መስራቾችና አንጋፋ መሪዎች፣ እነ ዶ/ር ዲማ ነግዎ፣ አቶ ሌንጮ ለታ የመሳሰሉት፣ የኦሮሞ ጥያቄ የመገንጠል ሳይሆን የዴሞክራሲ ጥያቄ ነዉ በሚል፣ ራሳቸውን ከኦነግ አግልለው፣ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፎረም (ኦዴፍ) የሚባል ድርጅት ማቋቋማቸውን ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ መግለጹዋ ይታወሳል::
ዘንድሮ በሚደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ለመሳተፍና ድርጅቱንም በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ወደ አዲስ አበባ እንዳቀኑ የገለጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ጉዳዩ ብዙዎችን ማስገረሙን ገልጸዋል::
በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ አማካኝነት በተለይ በሚኒሶታ የቀድሞ የኦነግ መሪዎችን ለማግባባት ከፍተኛ ሥራ ይሰራ እንደነበር ዘ-ሐበሻ ከዚህ ቀደም በፎቶ ግራፍ በተደገፈ ማስረጃ ስትዘግብ የቆየች ሲሆን በዶ/ር ዲማ ነገዎና በኦቦ ሌንጮ ለታ የሚመራው ኦዴፍ ለኦሮሞ ሕዝብ አዲስ የትግል ራዕይ አለኝ በሚል ሃገር ቤት ገብቶ ለመታገል መወሰኑንና ከዚህ በኋላም የኦሮሞ ሕዝብ ስለመገንጠል ሳይሆን በአንድነት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚኖርበትን መንገድ ፈጥሮ ለመታገል መወሰኑን መግለጹ ይታወሳል::
በቀጣዩ ዲሴምበር ወር አካባቢ አቶ ሌንጮ ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ በሰፊው ሲወራ የቆየ ቢሆንም ምክትላቸው ዶ/ር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ ቀድመው ገብተው ድርጅቱን በኢትዮጵያ ለማስመዝገብ እየተሯሯጡ ይገኛሉ ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ኦዲኤፍ በቀጣዩ ምርጫ እንደሚወዳደርም ጠቁመዋል:: ዶ/ር ዲማ ነገዎ በሽግግር መንግስት ወቅት በማስታወቂያ ሚ/ርነት ያገለገሉ መሆናቸው ይታወሳል::
ይህን ተከትሎ የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች በሚኒሶታ አካባቢ የሚገኙ ፖለቲከኞችን ያነጋገሩ ሲሆን የዶ/ር ዲማ ነገዎ አዲስ አበባ መግባትና የኦዲኤፍ በምርጫ መሳተፍ በገደል አፋፍ ላይ የነበረውን የወያኔ/ኢሕ አዴግ መንግስት ነብስ ይዘራበታል ሲሉ ይህን ውሳኔ ይተቻሉ:: እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉትም ኢሕ አዲኤግን በኃይል ለመጣል የመጨረሻው ሰዓት ላይ የደረሰ ቢሆንም የአቶ ሌንጮና የዶክተር ዲማ ኦዲኤፍ ኢትዮጵያ መግባት ኢሕ አዴግ ለሚፈልገው ና በምርጫ ስም ለሚያገኘው የፕሮፓጋንዳ ጥቅም አንድ አጋዥ ይሆንለታል ሲሉ ትችታቸውን ያስከትላሉ::
በሌላ በኩል የኦዲ ኤፍ ኢትዮጵያ መግባት ለኦሮሞና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ድል ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለይ እነዚህ የኦነግ መስራቾች የመገንጠል አላማቸውን ትተው በአንድነት ለመታገል መወሰናቸው ለሁሉም የምስራች ነው ይላሉ::
No comments:
Post a Comment