Saturday, August 3, 2013

ከጉራፈርዳ እስከ ጋምቤላ – የሁለት ሥርዓቶች ሰለባዎች

ከጉራፈርዳ እስከ ጋምቤላ – የሁለት ሥርዓቶች ሰለባዎች ከጉራፈርዳ እስከ ጋምቤላ – የሁለት ሥርዓቶች ሰለባዎች ‹‹የአማራ ብሔር ተወላጆች ዳግም ከጉራፈርዳ እየተፈናቀሉ ናቸው›› የሚለውን የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና አንብበው እየተገረሙ አንድ ትዝታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሙሉ ስማቸው እንዲገለጽ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አቶ ታደሰ ይባላሉ፡፡ አሁን የ56 ዓመት ጎልማሳ ናቸው፡፡ በተለይ የሰሜኑ ኢትዮጵያ በድርቅ በተደጋጋሚ በተመታበት 1977 ዓ.ም. ቀጣይ ዓመት በአሁኑ የደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ልዩ ስሙ ጉራፈርዳ ወደተባለ አካባቢ ተጉዘው ነበር፡፡ ‹‹ጥቅጥቅ ያለ ጫካ›› ነበር ወዳሉት ወደዚህ አካባቢ የተጓዙበትን ሁኔታ በትዝታ መልክ ይተርኩልኝ ጀመሩ፡፡ በደርግ ጊዜ ጋዜጠኛ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ነበሩ፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በወቅቱ የትግራይና የወሎ ክፍለ ሀገሮች በግድ ታፍሰው ለሚመጡ ሰፋሪዎች ቦታ ለማመቻቸት ወደአካባቢው ያመራውን አንድ የመንግሥት ቡድን ሥራ ለመዘገብ ነበር አብረው የተጓዙት፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሚዛን ቴፒ በመኪና ተጉዘዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በወቅቱ በመኪና መጓዝ አይታሰብም፡፡ በሔሊኮፕተር ለመጓዝ ተገዷል ቡድኑ፡፡ ‹‹ጥቅጥቅ ካለ ጫካ ውጪ ምንም ነገር አልነበረም፡፡ መሬቱ ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እርሻ የሚባል አያውቅም፡፡ በጠቅላላው ምንም ዓይነት ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ እንደተፈጠረ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ አቶ ታደሰ ትረካቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹ሰው ብሎ ነገርም የለም፡፡ አልፎ አልፎ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ጦር የያዙ ራቁታቸውን የሆኑ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ሆኖም ልብስ የለበሰ ሰው ሲያዩ የሚሸሹ ናቸው፤›› የሚሉት አቶ ታደሰ፣ በወቅቱ የተመለከቱት በትምህርት የሚያውቁት ‹‹የጋርዮሽ ማኅበረሰብ›› አኗኗርን ነበር ያስታወሳቸው፡፡ ሰፋሪዎች ወደ አካባቢው ከመንቀሳቀሳቸው በፊት የዩኒቨርሲቲ ዘማች ተማሪዎች የራሳቸውን መጠለያዎች ጨምሮ፣ ለሰፋሪዎች ጎጆ ቀለሱ ይላሉ የተመለከቱትን ሲያስታውሱ፡፡ በአካባቢው ከሁለት ሳምንታት በላይ የቆዩት አቶ ታደሰ በብዙ መኪኖች (መንገድ ተጠርጎ) በአካባቢው የተራገፉ የወሎ ሰፋሪዎችን ተመልክተዋል፡፡ ‹‹በቁጥር ብዙ ነበሩ›› ከማለት ውጪ በእርግጥ ቁጥራቸውን በውል መገመት አይችሉም፡፡ የማይተገበር ቃል አቶ ታደሰ ትዝታቸውን የጫረው ይኼው ዜና ቀደም ሲል በጉራፈርዳ ወረዳና በሌሎች ወረዳዎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ የመደበኛውም ሆነ የሶሻል ሚዲያ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ የሚዲያዎችን ቀልብ የሳበው በተለይ ቁጥራቸው በርከት ያለ (ከ22 ሺሕ በላይ) የአማራ ተወላጆች ለሦስት አሥርት ዓመታት ከነበሩበት፣ ካለሙት መሬትና ንብረት ካፈሩበት አካባቢ በአሰቃቂ ሁኔታ መፈናቀላቸው ነው፡፡ በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ሲፈናቀሉ የበለጠ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ የአካባቢ አስተዳደሮች እጅ አለበት ተብሎ የሚታመንበት የማፈናቀል ዕርምጃን በተመለከተ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም፣ ቁርጥ ያለ የፖለቲካ ውሳኔ የሚመስል ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ መንግሥት በነዋሪዎቹ ላይ በተፈጸመው ድርጊት እጅግ ማዘኑን ገልጸው፣ ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው ተመልሰው የሚሰፍሩበትና በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ የአስተዳደር አካላትም ሕግ ፊት ቀርበው እንደሚጠየቁ አጽንኦት ሰጥተው ነበር፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነትም ፈርጀዋቸው ነበር፡፡ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የወቅቱ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹አንዳንድ ሚዲያዎች ያጋነኑት›› በሚል ጉዳዩን የሚያሳንስ ምላሽ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን ወንጀል ፈጸሙ በተባሉ ግለሰቦች ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ መንግሥት ዛሬ ነገ ለሕዝብ ያሳውቃል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ነዋሪዎቹን ከቀያቸው የማባረርና የማፈናቀል ድርጊት ደግሞ ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተዘገበ ነው፡፡ በዚህ የማፈናቀል ድርጊት ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድም የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይም ክስ ለመመሥረት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡ በቅርቡ ቁጥራቸው በርከት ባለው በጉራፈርዳ ተፈናቃዮች ምክንያት ቀደም ብሎ አጀንዳ መሆን የቻለው ይኼው የመፈናቀል አደጋ፣ ሌሎች ጥያቄዎችንም የሚጭር ነው፡፡ ምናልባትም የጉዳዩ ስፋት በአስተዳደራዊ (ፖለቲካዊ) ውሳኔዎችና በፍርድ ቤት ክትትል ብቻ እንደሚፈታ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ጉራፈርዳ – ከግዳጅ ሰፈራ ወደ መፈናቀል በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት ያካሄደ ድርጅት ወይም ግለሰብ ማግኘት ባይቻልም፣ አንዳንድ ከደቡብ ክልል መንግሥት የተገኙ መረጃዎች ሁኔታውን ለመረዳት የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ በጽሑፉ መግቢያ ላይ የሰፈራ አጀማመሩን የተረኩልን አቶ ታደሰ እንዳሉት፣ የአማራ ብሔር ተወላጆች ወደ አካባቢው የተወሰዱት በ1978 ዓ.ም. በፈቃደኝነት ላይ ባልተመሠረተ የደርግ የሰፈራ ፕሮግራም ነበር፡፡ የቀድሞው መንግሥት እጅግ ከሚተችባቸው ድርጊቶች አንዱ በሆነው የግዳጅ ሰፈራ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይ ደግሞ ከወሎ አካባቢ (የአማራ ተወላጆች) የመጡ ዜጎች በቤንች ማጂ ዞን፣ በጉራፈርዳ ወረዳና በሰሜን ቤንች ወረዳ ሰፍረው ይኖሩ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ የተወሰኑት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ቀድሞ ወደመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ሌሎች ግን እዚያው ይቀራሉ፡፡ አካባቢውን ለቀው ወደመጡበት አካባቢ ተመልሰው የነበሩትም ቢሆኑ፣ ከአሥር ዓመት በኋላ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ የአካባቢውን ለምነትና አጠቃላይ የተፈጥሮ ሁኔታ ያውቁ ስለነበር ተመልሰው መስፈሩን ተያያዙት፡፡ ይህ እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ የቀጠለው የመንግሥት ‹‹ዕውቅና›› ያልነበረው መልሶ የመስፈር ሁኔታ፣ በተለይ የጉራፈርዳ ወረዳን የሚመለከት ነው፡፡ ከቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ቃለ ምልልስ መረዳት እንደሚቻለው፣ በወቅቱ ወደ አካባቢው የመጡት ሰዎች በአካባቢው የመንግሥት አካላት በሕጋዊ መንገድ ስምሪት አግኝተው ወደ ልማት የገቡ አልነበረም፡፡ ሰፈራው በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩና በአካባቢው ‹‹ነባር›› ነዋሪዎች ላይ ጫና ፈጥሯል የሚለው የክልሉ መንግሥት አቋም ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ከ2000 እስከ 2001 ዓ.ም. ባደረገው ጥናት በደን ምንጠራና ሰው ያልሰፈረበትን ክፍት ቦታ በመቆጣጠር ሦስት ወረዳዎች ላይ ነዋሪዎቹ ሰፍረዋል፡፡ እነሱም ጉራፈርዳ፣ ሜኤኒት ጎልዲያና ሜኤኔት ሻሸ ይባላሉ፡፡ በጥናቱም መሠረት በጉራፈርዳ ወረዳ ብቻ 22,046 ሰዎች የሰፈሩ ሲሆን፣ በተቀሩት ሁለት ወረዳዎች ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች ሰፍረዋል፡፡ በጉራፈርዳ ከሰፈሩ ሰዎች መካከል ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺሕ የሚጠጋውን ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር በመነጋገር በባህር ዳር ማስፈር መቻሉ ይነገራል፡፡ የተቀሩትም ለእርሻ ሁለት ሔክታር፣ ለመኖርያ ቤት መሥሪያ አንድ ሺሕ ካሬ ሜትር እንዲሰጣቸው መደረጉን የክልሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መሠረታዊ መብቶች በቀድሞ ሥርዓቶች የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ‹‹ብሔራዊ ጭቆና›› ደርሶባቸዋል የሚለው ብዙም የሚያከራክር አይደለም፡፡ በመሆኑም በ1986 ዓ.ም. በፀደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሆኖ ተወስኖአል፡፡ ክልሎች ቋንቋን ጨምሮ የሚተዳደሩበት የራሳቸው ሕገ መንግሥትም እንዲያፀድቁ ጭምር ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በአገሪቱ የሕጎች ሁሉ ሕግ (እናት) የሆነው ይኼንን የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትና ሌሎች የክልል ሕገ መንግሥቶችንም ለማስፈጸም በየጊዜው የሚደነገጉ ሌሎች ሕጎች፣ አዋጆችና ድንጋጌዎች የሕገ መንግሥቱን ዋነኛ መርህ ሊጥሱ አይችሉም፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ንፍቀ ክበብ ውጪም መተርጎምም የለባቸውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ የመሠረት ድንጋይ የሆኑት የብሔር ብሔረሰቦች መብትና የሰብዓዊ መብቶች ቃል ኪዳን ናቸው፡፡ በአንቀጽ 39 ላይ የሰፈረው የብሔር ብሔረሰቦች መብት እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ማንነቱን የማክበር፣ ቋንቋውን የመጠቀም (በአፍ መፍቻ ቋንቋውን የመማር)፣ ታሪኩንና ባህሉን የማሳደግና የመግለጽ፣ እንዲሁም የመጠበቅ መብት ሰጥቶታል፡፡ ይህ በቡድን መብት የሚጠቃለል ሲሆን፣ አንድ ዜጋ ሕገ መንግሥቱ ከሰጠው ዋስትና አንዱ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመሥራት፣ የመኖርና ንብረት የማፍራት ይገኝበታል (አንቀጽ 32)፡፡ ይህንን ንብረት የማፍራት፣ የመጠቀምና የመገልገል መብቶች በአንቀጽ 40 በስፋት የተዘረዘሩ ሲሆን፣ በሌሎች አንቀጾች የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብትና መሬት የኢትዮጵያ ዜጎችና የመንግሥት ንብረት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በአንቀጽ 44 እንደተደነገገውም፣ መንግሥት በሚያካሂደው ልማት ምክንያት በቂ ካሳ አግኝተው ከቦታ ቦታ የሚፈናቀሉ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማንኛውም ዜጋ የሕይወቱና የንብረቱ ደኅንነት ተጠብቆ የመኖር መብቱ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቶች የሚዲያ ትኩረት ያገኘው የአማራ ተወላጆች በደቡብ ክልል የጉራፈርዳና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሰፋሪዎች የመፈናቀል ጉዳይ ቢሆንም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ኦሮሚኛ ቋንቋ የማይችሉ ሰዎች የመሥራት መብታቸው እየተገደበ እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ በመሆኑም በአካባቢው የሚገኙት ቁጥራቸው ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የአማራ ተወላጆችና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የትግራይ ተወላጆች ቋንቋውን ባለመናገራቸው ምክንያት ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑንና መኖሪያቸውን ጥለው የሚወጡ መኖራቸው ይነገራል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሁን የአማራ ክልል ወደሆነው አካባቢ የተንቀሳቀሱ የኦሮሞ ተወላጆች የራሳቸውን ዞን መሥርተው ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እየተጠቀሙ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ በርካታ የአማራ ተወላጆች ይህንን መብት አልተጎናፀፉም በማለት ወቀሳዎች ይቀርባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በቀደሙት ሥርዓቶች በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ጭምር በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ ደገኞች (ትግራይና አማራ) በአካባቢው አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ተወስኖ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ የመመረጥና የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ መብት እስከመከልከል የሚደርሰ ድንጋጌ የነበረ ሲሆን፣ ይህ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት በተወሰነ መልኩ ሊስተካከል ችሏል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የአናሳዎች መብት (Minority Right) እስከ ዞን ደረጃ የራሳቸውን አስተዳደር የመመሥረት መብት ያጎናፅፋቸዋል፡፡ ሆኖም በአጠቃላይ በክልላቸው ባላቸው ቁጥር ብዙኃን (Majority) የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ግን በተለያዩ ‹‹የታሪክ›› አጋጣሚዎች በሌሎች አካባቢዎች አናሳ ሆነው የሚገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች በአማራ ክልል አናሳዎች ሲሆኑ፣ የአማራና የትግራይ ተወላጆች ደግሞ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች አናሳ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በ2007 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የቀረበው አንድ የባለሙያዎች ጥናት ይህንን የሚመለከት ነው፡፡ በመሆኑም አገራዊ ኮንፈረንስ ተደርጎ ውይይት እንዲደረግበትና በኅብረተሰቡ መካከል ግልጽነት እንዲፈጠር ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ‹‹Report of the Independent Expert on Minority Issues፡ Mission to Ethiopia›› በሚል ሚስስ ጋይ ማክ ደጋል አደንዱም በተባሉ ባለሙያ የቀረበው አንድ ሰፊ ጥናታዊ ሪፖርት፣ ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ስለሚገኙ ንዑሳን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው ምንም የሕግ ከለላ የለም ይላል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ጨርሶ የፖለቲካ ተሳትፎ የተነፈጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመኖራቸውን ያህል፣ አንዳንድ አናሳ ብሔረሰቦች ደግሞ ቋንቋቸው በመጥፋት ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳስባል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ የከፋ ችግር ባይኖረውም በብሔር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያላግባብ እየተተረጎመ የራስን መብት ከመጠበቅ አልፎ የሌሎችን መብት ለማፈን ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ በስፋት ትችት ይቀርባል፡፡ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሕገ መንግሥታዊ አንቀጾች ማናቸውም ዜጋ በአገሪቱ ተዘዋውሮ በነፃነት የመሥራትና የመኖር መብት ያለው ቢሆንም፣ ይህ መብት በተግባር ሲጣስ እየተስተዋለ መሆኑም እንዲሁ፡፡ ምናልባትም አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሕገ መንግሥቱ ከዚሁ በፊት ብሔራዊ ጭቆና ለደረሰባቸው ብሔረሰቦች ሙሉ መብት ያጎናፀፈ ቢሆንም፣ እነዚህን ወገኖች የሚመለከት ግን ግልጽ የሆነ የሕግ ከለላ የለም፡፡ አቶ ታደሰ እንደተመለከቱት፣ ‹‹ደገኞች›› በግዳጅም ሆነ በውዴታ ኑሮአቸውን ለማሻሻል በተንቀሳቀሱበት አካባቢ ከመጡበት ማኅበረሰብ ባመጡት በእርሻ፣ በቤት አሠራር፣ የተለያዩ ምርቶችን በማምረትና በተለየ አኗኗር ዘይቤ ጠቃሚ ልምድ ያበረከቱ ናቸው፡፡ ይህንን በታሪክ አጋጣሚ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ መዘንጋት እንደሌለበትም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በቀደሙት መንግሥታት አስገዳጅነት የተፈናቀሉ ወገኖች፣ የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች ሕገ መንግሥቱን አዛብተው በመተርጎማቸው ምክንያት ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን፣ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ካላደረገበት ችግሩ መቆሚያ እንደሌለው የሕግ ምሁራንም ያስረዳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment