To breathe Democracy in Ethiopia , lets us fight together for our Freedom and Justice !!!!!
Friday, August 30, 2013
August 30, 2013 “ ከአድባይነት እርግማን ይሰውረን!”
ከአህያ ጋር ብጣሪ በልታ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች
የሃይማኖት መሪው ቡድሐ የሚሰጠን አንድ እንቆቅልሽ የሚከተለውን ይመስላል። አንድ ነጋዴ ሩቅ ሄዶ ሲመለስ፤ ቤቱ በሽፍቶች ተዘርፎና ተቃጥሎ ይደርሳል፡፡ ከቤቱ ከተረፈው ረመጥ – መካከል አንድ ተቃጥሎ የከሰለ የሰው ገላ ያያል፡፡ “ይሄ ትንሹ ልጄ መሆን አለበት” አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ምርር ብሎ አለቀሰ፡፡ ደረቱን መታ፡፡ ፀጉሩንም ነጨ፡፡ ገላውን እንደገና የማቃጠል፤ የሐዘን ሥነ-ስርዓት እንዲካሄድም አደረገ፡፡
ይህ ወንድ ልጁ ነው፡፡ ከልጁ የናፍቆት ስሜት ለመላቀቅ በጭራሽ ካለመፈለጉ የተነሳ፣ ለቅጽበት እንኳ ሳይለየው የልጁን አስከሬን አመድ በከረጢት አንጠልጥሎ ይዞር ጀመር፡፡ ቆይቶም ከሀር የተሰራ ከረጢት አሠርቶ ይሸከመው ጀመር፡፡ ቀን ከሌት ይዞት ይዞራል፡፡ ሥራም ቦታ ቢሆን ተሸክሞት ይውላል፡፡ በእረፍት ሰዓቱም እንደዚያው፡፡ ከአመዱ የሚለይበት አንዳችም ደቂቃ የለም፡፡
አንድ ሌሊት፤ ለካ ወንድ ልጁን ሽፍቶቹ አግተው ወስደውት ኖሮ፤ ከታሠረበት አምልጦ አባቱ አዲስ ወደ ሠራው ቤት ይመጣል፡፡ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ላይ ደርሶ፤ የአባቱን ቤት በር በስሜት ፍንድቅድቅ ብሎ አንኳኳ፡፡ አባቱ፤ አሁንም የከረጢት አመዱን እንደተሸከመ ነው፡፡ “ማነው፤ በዚህ ሌሊት የሚያንኳኳው?” አለና ጮኾ ጠየቀ፡፡ “እኔ ነኝ ወንድ ልጅህ ነኝ አባባ” አለ ልጁ፤ በበሩ ሽንቁር እያየ
“አንተ ባለጌ ሰው፤ አንተ “የእኔ ልጅ ልትሆን ከቶ አትችልም፡፡ የእኔ ልጅ ከሶስት ወር በፊት ሞቷል፡፡ አመዱ እዚሁ እጄ ውስጥ አለ” አለው፡፡ ትንሹ ልጅ ግን በሩን መደብደቡን ቀጠለ፤ ጮኾ፤
“ኧረ አባባ እኔ ያንተው ልጅ፣ የምታውቀኝ ውዱ ልጅህ ነኝ፤ አስገባኝና እየኝ!” ደጋግሞ ለመነው፤ ተማጠነው፤ አባትዬው ግን፤ “ዘወር በል ብዬሃለሁ! ከዚህ ወዲያ አልታገስህም፡፡ ድራሽህ ይጥፋ! አለዚያ ብትንትንህን ነው የማወጣህ”
ለመጨረሻ ጊዜ ልንገርህ፤ የእኔ ልጅ በሽፍቶች ተቃጥሎ ሞቶ፣ እኔ አስከሬኑን አመድ አድርጌ፣ አመዱን ተሸክሜ ስዞር ከርሜያለሁ፡፡ ስለዚህ አንተ የመጣኸው የልጄን ሐዘን ዳግመኛ ለመቀስቀስና የእኔን አንጀት ለማቃጠል ነው! አንት ጨካኝ አረመኔ፤ ጥፋ ከፊቴ ይለዋል። ልጅየው ተስፋ ቆርጦ ሰፈሩን ጥሎ ጠፋ፡፡ አባት፤ በህይወት ያለ እውነተኛ ልጁን ለአንዴም ለዘለዓለም አጣ፡፡* * *እንደ ቡድሐ አመለካከት፤ ከአንድ አስተሳሰብ ጋር እኝኝ ብለን ከተጣበቅንና “አንዱና አንዱ እውነት” ይሄ ብቻ ነው ብለን ካከረርን፣ እውነተኛውን እውነት የማወቅ እድላችንን እንዘጋለን። እውነት እንድ ሰው ደጃፋችሁ ቆሞ ቢያንኳኳም እንኳ የአዕምሮአችሁን በር ለመክፈት ዝግጁ አትሆኑም፡፡ ስለዚህ ስለ አንድ እውነት የምትገነዘቡበትን መንገድ ሥራዬ ብላችሁ መርምሩት፡፡ ተጠንቀቁ፡፡
የነገር ሁሉ መጀመሪያው፤ ከሃሳብ እሥር ነፃነትን ማወጅ ነው፡፡ ይህን እውነት ወደ እኛ አገር ፖለቲካ ስንመነዝረው፤ ቁልጭ ያሉ አመድ የማቀፍና ህያው ልጅን የመካድ፤ እውነታን እናገኛለን፡፡ እውነተኛውን ልጃችንን እንለይ፡፡ በከረጢት ውስጥ ያለው አመድ በህይወት ካለው ልጅ የተለየ መሆኑን እርግጠኛ እንሁን፡፡ ከአመዱ ከግትር ሃሳባችን እንገላገል፤ እኛ የጀመርነው መንገድ ብቻ ነው ዳር የሚያደርሰው ብለን ድርቅ ከማለት አባዜ ተላቀን የጀመርነው መንገድ መጨረሻ የማያሳልፍ -ግድግዳ (Dead End) ቢሆንስ? አብረውን ከሚጓዙት መካከል ሃሳባቸውን የሚለውጡ ቢገኙስ? የመኪናው ጐማ ቢተነፍስስ? የባቡሩ ሃዲድ ቢጣመምስ? ብለን እንጠይቅ።
አንድ የአገራችን ፀሐፌ ተውኔት እንዳለው፤ “ገና ላልተወለደ ልጅ ሥም እናውጣ ብለን ለምን እንጣላለን፡፡“ዐይናማው” ብለነው እውር ሆኖ ቢወለድስ? ክንዴ ብለነው እጁ ቆራጣ ቢሆንስ?…” ብለን መጠራጠር ቢያንስ ከጭፍንነት ያድነናል። ከአንድ መሥሪያ ቤት በሙስና፣ በፍትሐዊነት ወይም በኢዲሞክራሲያዊነት፤ በግምገማ የተነሳን ሰው ለሌላ መሥሪያ ቤት በኃላፊነት ማስቀመጥ አልሸሹም ዞር አሉ፤ ነው፡፡
ይሄኛው መሥሪያ ቤት አንቅሮ የጣለውን ግለሰብ ያኛው መሥሪያ ቤት በምን ዕዳው ይሸከማል? የሀገሪቱን የሥራ ሂደት ባለቤቶች በበኩር ልጅነት አቅፈንና “የባለቤቱ ልጅ” አሰኝተን ስናበቃ በሀቅ የሚለፉላትን ሀቀኛ ልጆች በር እያንኳኩ ሳንከፍት እያባረርናቸው ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት ይቻለናል?
በቡድናዊና ድርጅታዊ መንፈስ፤ እስከመቼ እከክልኝ፤ ልከክልህ ተባብለን እንዘልቀዋለን?“እብድ ሆኜ ስለማላውቅ፣ እብድ የሚያስበውን አላውቅም፤ ዝም፣ ጭጭ ብለህ ተቀምጠህ ሳይህ ምናልባት ይሄ እብደትህ ልዩ ሰላም ሰጥቶህ ይሆንን? ብዬ እቀናብሃለሁ፤ መንሳፈዊ ቅናት ማለቴ ነው” ይላል የአገራችን ፀሐፊ፡፡
ዝምታ ማስቀናቱ ይገርማል፡፡ ስንት ግፍ ሲሰራ እያየህ ዝም ስንት ዘረፋ ሲካሄድ እያየህ ዝም፤ ጓዳህ እየተራቆተ፤ ኢኮኖሚህ እየተንኮታኮተ እያየህ ዝም ለማለት ከቻልክ የሚያስቀና ዝምታ አለህ፤ ታድለሃል ማለት ነው፡፡ ከእብደት ውስጥ የሚገኘው ልዩ ሰላም ይሄ መሆኑ ነው፡፡ ዝም የሚሉ ያሉትን ያህል፣ ሃያ አራት ሰዓት በመለፍለፍ እኛ ነን ጀግና የሚሉም አገራችን ያፈራቻቸውና በተገለባባጭነት፣ በአድር ባይነት፣ በጥገኝነት ንፍቀ – ክበብ ውስጥ የሚኖሩ አያሌ “ቀልጣፋ” ሰዎች አሉ፡፡ ከጠቆረው መጥቆር፣ ከነጣው መንጣትን ተክነውበታል፡፡“እንደ ወዶ-ገባ ኮርማ፣ ተነስ ሲሉት የሚነሳ፤ ተኛ ሲሉት የሚተኛ!” ያለው ዓይነት ነው ገጣሚው፡፡
ከየትኛውም ማዕድ ለመቋደስ እጃቸውን (የዓለም የእጅ መታጠብን ቀንን እያከበረ እንደማለት) ታጥበው፣ ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ ናቸው፡፡ ለእነሱ ፖለቲካ በየትኛውም የሳንቲሙ ገጽ – ማለትም በአውሬውም በሰዉም በኩል – ለመጠቀም የሚችሉ ናቸው፡፡ መቼም ቢሆን መቼም በየትኛውም ገዢ ዘመን አድርባይነታቸውን አያቋርጡም። The pendulum of opportunism never stops oscillating እንዳለው ነው ሌኒን፡፡ “ከአህያ ጋር ብጣሪ በልታ፣ ከፈረስ ጋር ገብስ ትበላለች” ይለዋል የወላይታው ተረት፡፡ ከአድባርባይነት እርግማን ይሰውረን!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment