Saturday, August 3, 2013

በግብረሰዶም ተጠርጣሪዎች ላይ የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ የምስክርነት ቃል ሰጡ

በግብረሰዶም ተጠርጣሪዎች ላይ የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ የምስክርነት ቃል ሰጡ ሪፖርተር የማስተካከያ ዘገባ እንዲሠራ ታዘዘ ሁለት የ10 እና የ11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የግብረሰዶም ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ ስድስት መምህራን ክስ ላይ፣ ከዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በተጨማሪ አንዲት የሳይኮሎጂና የሳይካትሪ ባለሙያ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የሙያ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ በማየት ላይ ያለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰባተኛ የወንጀል ችሎት፣ ስማቸው በሚዲያ እንዳይገለጽ የከለከለላቸው የሳይኮሎጂስትና የሳይካትሪ ባለሙያዋ፣ በተጠርጣሪ መምህራን የግብረሰዶም ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባሉትን ሁለት ወንድ ሕፃናት፣ ለሦስት ጊዜያት አግኝተው እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹንም ሆኑ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው የተባሉት ሕፃናትን እንደማያውቋቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ሕፃናቱን ከአራት ወራት በፊት ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ታዘው ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለሙያዋ ከሕፃናቱ ጋር ቃለ መጠይቁን ያደረጉት፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በፖሊስ ጣቢያ መሆኑን ጠቁመው፣ መጀመሪያ ከእናቶቻቸው ጋር ቀጥለው ደግሞ ሕፃናቱን ለብቻቸው ማነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሕፃናቱን መጀመሪያ ከወላጆቻቸው ጋር ያነጋገሯቸው ስለማያውቋቸው ለመለማመድ መሆኑንና ቀጥለው ለብቻቸው ቤተሰቦቻቸውን ሳይፈሩ እንዲያነጋግሯቸው ማድረጋቸውን የገለጹት ባለሙያዋ፣ በምክር ወይም ድርጊቱን በማስጠናት የተሳሳተ ማስረጃ እንዳይሰጧቸው፣ ቃለ መጠይቁን ያደረጉላቸው እያጫወቱና ዘና እንዲሉ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠዋት ቁርሳቸውን ከበሉበት እስከ ማታ ከትምህርት ቤት ተመልሰው ወደ ቤታቸው እስከሚገቡበት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ያደረጉትን አንድ በአንድ እንዲያስረዷቸው በመጠየቅ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ባለሙያዋ የሚፈልጉትን በጨዋታ ዓይነት ተጎጂ የተባሉት ሕፃናት ምንም ሳይፈሩ የጠየቋቸውን ሁሉ በአግባቡ እንደመለሱላቸው አክለዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ያንኑ ጥያቄ ሲጠይቋቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ማስረዳታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ሕፃናቱ እንዴት ቀናቱን ሊያስታውሱ እንደሚችሉ ተጠይቀው ባለሙያዋ ሲመልሱ፣ ሕፃናቱ ቀኑን በትክክል ባያስታውሱም ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ጊዜ በዓል ካለ ወይም በዚያን ጊዜ የማይረሳ ነገር ካለ እሱን በማስታወስ እንዲያስታውሱት ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ከተጠቂዎቹ አንዱ ቀኑን በደንብ አስታውሶ እንደነገራቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ያሏቸውን ሰዎች ስምና ድርጊት እንዳስረዷቸው ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት ከድርጊቱ በኋላ የሚያሳዩት ባህሪ ካለና የጉዳዩ ባለቤት በሆኑት ሕፃናት ላይ ያዩት የባህሪ ለውጥ ወይም ምልክት ካለ እንዲያስረዱ ተጠይቀው፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሕፃናት አራት ባህሪያትን ያሳያሉ፡፡ ፈሪ፣ ኃይለኛ (ተደባዳቢ)፣ ብቸኛ መሆንን መፈለግና ከፍተኛ የሆነ የወሲብ ፍላጎት የማሳየት ባህሪያት እንደሚያመጡ አስረድተዋል፡፡ ሌላው በትምህርት ላይ የሚያሳዩት ሁኔታ ሲሆን፣ በአንድ ትምህርት ላይ ብቻ ጎበዝ የመሆንና ሌላውን የመጥላት ወይም ፍላጎት ያለማሳየትና ደብተራቸውን ጥሎ የመምጣት ባህሪም እንደሚያመጡ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡ ተጠቂ ከተባሉት ሁለቱ ሕፃናት አንደኛው የወሲብ ፍላጎት እንዳለውና እሱም እንዳረጋገጠላቸው የገለጹት ባለሙያዋ፣ ይኼ ስሜት ሲመጣበት ከማን ጋር ለማድረግ እንደሚፈልግ ጠይቀውት፣ ከወጣት ወንዶችና እንደ አስተማሪዎች ካሉ ወንዶች ጋር ማድረግ እንደሚፈልግ፣ ወንድ ሕፃናትና ትልቅ ሰው እንደማይፈልግ እንዳስረዳቸው ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ጥያቄ ያቀረቡለት በጥናት ሕፃናት የሚጠቁት በአብዛኛው በሚያውቁትና በቤተሰብ፣ ወይም ዘመድ መሆኑን ስለተረጋገጠ በቤታቸው ውስጥ ወንድሞችና አባት ስለሚኖሩ ከነሱ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment