ኀዳር ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ከአለማቀፍ የግል ባንኮች ለመበደር የወሰነው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ለግል አበዳሪ ተቋማት ባላሃብቶች የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየቶችን እየሰጡ ነው።
ፋይናንሻል ታይምስ 1 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ጫፍ ላይ የደረሰው መንግስት ለውጭ ባለሀብቶች የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ያልተለመደ ወይም እስከዛሬ ያልታየ ነው ብሎታል።
አገሪቱ በኢኮኖሚ እየገሰገሰች መሆኑዋን፣ በምግብ ራሱዋን መቻሉዋን፣ ሰላምና መረጋጋቱ አስተማማኝ ደረጃ ላይ መድረሱን በአጠቃላይ ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ እየሆነ መሆኑን በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን የሚገልጸው መንግስት፣ ሚስጢራዊ በሆነ መልኩ ለባላሀብቶች ያቀረበው እና የፋይናንሻል ታይምሱ ዣቪር ብላስ የተመለከተው 108 ገጽ ሪፖርት ፣ እስከዛሬ በመንግስት የሚባለውን ሁሉ የሚያፈርስ ነው። ሙሉውን ሪፖርት ለመመልከት ኢሳት ባይችልም፣ የሪፖርቱ ቅጅ ፋይናንሻል ታይምስ እጅ እንደሚገኝ ጋዜጠኛ ዣቪል ለኢሳት በኢሜል በላከው መልእክት አረጋግጧል።
መንግስት የውጭ ኢንቨርስተሮች ለኢትዮጵያ ብድር ከመፍቀዳቸው በፊት ሊያዉቋቸው ይገባል ያላቸው ነጥቦች ከፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከረሃብና ከጦርነት ጋር የተያያዙ ናቸው።
ባለሀብቶች ከኤርትራ ጋር ጦርነት እንደገና ሊያገረሽ እንደሚችል አስቀድመው ማወቅ አለባቸው ያለው መንግስት፣ ከጅቡቲ ጋር ያለው ግንኙነት በሆነ ቢሻክር ጅቡቲ ወደቡዋን ልትዘጋ የምትችለበት አጋጣሚ እንደሚኖርም ልብ ሊሉ ይገባል ብሎአል። በተለይ መጪውን ምርጫ ተከትሎ መንግስት ምርጫው በሰላም ይጠናቀቃል ብሎ ቢያስብም፣ ግጭትና አለመረጋጋት ሊከሰት እንደሚችል ባለሃብቶች ከወዲሁ ማወቅ እንዳለባቸው አሳስቧል።
በአገሪቱ ውስጥ ረሃብ ሊነሳ የሚችልበት አደጋ አለ ያለው የኢህአዴግ መንግስት፣ ከፍተኛ የሆነ ድህነት እንዳለም ሊያዉቁት እንደሚገባ አሳስቧል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰው ልማት መስፈረት ኢትዮጵያ ከ187 አገራት በመጨረሻዎቹ ተርታ ከሚገኙት አገራት በ173ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አበዳሪዎች ሊያዉቁት እንደሚገባ አስጠንቅቆ፣ መንግስት ከፍተኛ ሆነ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመውም አልሸሸገም። በተለይ የአገሪቱ የመጠባበቂያ ገንዘብ ( hard currency reserve) እያስቆለቆለ በመሄዱ ፣ በአሁኑ ሰአት አገሪቱ ለሁለት ወር ብቻ የሚበቃ የመጠበባቂያ ገንዘብ እንዳላትም ይፋ አድርጓል።
መንግስት በሪፖርቱ ከቻይና ጋር ስላለው ግንኙነትም ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱት ግንባታዎች ቻይና ወነኛዋ አበዳሪ አገር መሆኑዋን መንግስት ገልጾ፣ አምና ከውጭ ከተገኘው ብድር ውስጥ 69 በመቶው፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ዘንድሮ ከተገኘው ብድር ውስጥ 42 በመቶው የቻይና መሆኑን ጠቅሷል። ዜድ ቲኢ፣ ሃዊይ እና የቻይና ኤልክትሪክ ኩባንያ ባለፉት ጥቂት አመታት 2 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ በመስጠት ስራውን እርሳቸው እየሰሩ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
አበዳሪ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገጥማቸው ነገር ማስጠንቀቂያ በግልጽ ቢሰጣቸውም፣ ለኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮዮን ዶላር ብድር ለመፍቀድ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። ይህም የሆነበት ምክንያት የአሜሪካ፣የእንግሊዝ፣ የአውሮፓ ህብረትና የጃፓን ቱጃሮችና ኩባንያዎች በእነዚህ አገራት ባንኮች ገንዘባቸውን በማስቀመጥ የሚያገኙት ወለድ እጅግ አነስተኛ መሆን፣ የመክሰር አደጋ ላለባቸው አገሮች በድፍረት በማበደር እድላቸውን ለመሞከር መፈለጋቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
በገንዘብ ኢኮኖሚ ላይ በሚሰጡት አስተያየት የሚታወቁት ፕ/ር ሰኢድ ሃሰን የምእራብ አገራት ባለሃብቶች ከባንኮች የሚያገኙት ወለድ ወደ ዜሮ እየተጠጋ መምጣቱ ብድሩን ለመፍቀድ ሳይገፋፋቸው እንዳልቀረ ለኢሳት በኢሜል በመግለጽ የፋይናንሻል ታይምስን አስተያየት አጠናክረዋል።
መንግስት በአገር ውስጥ ሁሉም ጥሩ እንደሆነ እየተናገረ በድብቅ እንዲህ አይነቱን አስደንጋጭ ሪፖርት ለምን ለማውጣት ፈለገ የተባሉት ፕ/ር ሰኢድ፣ የተለያዩ መላ ምቶችን አቅረበዋል። መንግስት የውጭ አማካሪ ድርጅቶችን በመቅጠር ሪፖርቱን ሳያዘጋጅ እንዳልቀረ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ የውጭ አማካሪ ድርጀቶች ደግሞ እያንዳንዷን ችግር በግልጽና ተአማኒነት ባለው ሁኔታ የማቅረብ ግዴታ ስላለባቸው ሪፖርቱን በዚህ መልክ አቅረበውት ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በሌላ በኩል መንግስት ምን ማቅረብ እንዳለበት ባለማወቁ ወይም እውነታውን ሳልደብቅ ባቀርብ ባለሃብቶችን ለማረጋጋት ይጠቅመኛል ብሎ አስቦ ሊሆን እንደሚችል ፕ/ር ሰኢድ ገልጸዋል።
ዋናው መታወቅ ያለበት ይላሉ ፕ/ር ሰኢድ፣ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ ያጋጠመው በመሆኑ ታላለቅ ፕሮጀክቶች ቆመዋል። “እነዚህ ፕሮጀክቶች ለመጨረስ ገንዘብ ይፈልጋል፣ ፕሮጀክቶቹ ደግሞ ህዝቡን በመደለል ስልጣን ላይ ለማቆየት የሚጠቀምባቸው ናቸው፣ ከዚህም በተጨማሪ ለህወሃቶች ፕሮጀክቶቹ ገንዘብ እንደልብ የሚዘርፉባቸው በመሆኑ እንዲቆሙ አይፈለገም” ያሉት፣ ፕ/ር ሰኢድ፣ ስራው ከተስተጓጓለ መንግስትን ለካድሬዎቹ እንደልቡ ሊርጭላቸው የሚችል ገንዘብ ስለማይኖረው ከእነዚህ ፕሮጀክቶች የሚጠቀሙት ካድሬዎች መንግስትን ይከዳሉ ስለዚህም መንግስት የፈለገውን ዋጋ ያስከፍል በማንኛውም መንገድ ገንዘብ ለመበደር” መቁረጡን እናያለን ሲሉ አክለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ይላሉ ፕ/ር ሰኢድ መንግስት ከቻይና ለመበደር ፈተና ያጋጠመው በመሆኑ ኢህአዴጎች ከቻይና ጥገኝነት ለመላቀቅ ተጨማሪ ብድር የሚያገኙባቸውን ተቋማት ማፈላለጋቸው እንዲሁም ከቻይና ኩባንያዎች የሚያገኙት አገልግሎት ደረጃውን ያልጠበቀ መሆንና ከቻይና ጋር ቢዝነስ መስራት ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን እየተረዱ በመምጣታቸው ፊታቸውን ወደ ግሉ ገበያ ለማዞር ሳይገደዱ አልቀረም።
ከግል ተቋማት መበደር ጠቃሚ ነገር ቢኖርም፣ ገንዘቡ አትራፊ ሊሆኑ በሚችሉ ድርጀቶችና ሙስና አነስተኛ በሆኑ ተቋማት ጥቅም ላይ መዋል ይገባል ሲሉ ፐሮፌሰር ሰኢድ ይመክራሉ። መንግስት ያልተለመዱ አደጋዎችን በመዘርዘር ምናልባትም የሙስናና የምርታማነት ችግሩን ለመሸፋፈን የተጠቀመበት አካሄድ ሊሆን እንደሚችልም ፕ/ሩ ለኢሳት በላኩት የኢሜል መልእክት ገልጸዋል።
ጊዜውን በትክክል ማስቀመጥ ባይቻልም ኢትዮጵያ እዳዋን ለመክፈል ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥማት የገለጹት ፕ/ር ሰኢድ፤ ከግል አበዳሪ ተቋማት ገንዘብ ሲበደሩ ብደሩን እስከወለዱ መክፈል የሚጀመረው ወዲያውኑ በመሆኑ አንዱ ፈተና ነው ይላሉ። ወለዱ አይኤም ኤፍና የአለም ባንክ ከሚያበድሩት ጋር ሲተያይ ከፍተኛ መሆኑ እንዲሁም ብድሩ ተከፍሎ የሚጠናቀቅበት ጊዜ አጭር መሆኑ ሌላው ፈተና ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የንግድ ሚዛን ጉድለት መስፋት ተጨማሪ ፈተናዎች ናቸው።
ብድሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስና ለመንግስት የፖለቲካ ትርፍ ለማስገኘት ቢጠቅምም፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያባብሰዋል። በሌላ በኩል ግን ይላሉ ፕሮፌሰር ሰኢድ መንግስት መሰረታዊ የሆነ የመዋቅር ለውጥ ካላደረገ ብድሩ የመንግስትን እድሜ ሊያሳጥር ይችላል። በሁሉም አማራጮች መንግስት አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወቱን ፕ/ር ሰኢድ ገልጸው፣ በአጠቃላይ መንግስት ፊቱን ወደ ግል አበዳሪ ተቋማት ማዞሩ የ5 አመቱ የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ከፍተኛ ውድቀት የሚያሳይ ነው ሲሉ አጠቃለዋል።
No comments:
Post a Comment