Monday, May 19, 2014

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ክለላ ዛሬ በድብቅ ሊፈረም ነው! – አብርሃ ደስታ

የኢትዮ ሱዳን ዳር ድንበር በግልፅ የተከለለ እንዳልሆነ ይታወቃል። የኢትዮጵያ አርሶአደሮች የሚጠቀሙት መሬት የኢትዮጵያ እንደሆነ ሲወሰድ ሱዳናውያን የሚገለገሉበትም የሱዳን ነው ተብሎ ይታሰባል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያውያን አርሶአደሮችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ለሱዳን ማስረከቡ ይታወቃል። ብዙ የኢትዮጵያ አርሶአደሮች ተፈናቅለዋል፣ የተወሰኑ ተለዋጭ መሬት ሲሰጣቸው ምንም ያላገኙም አሉ።
SUDANድንበሩ ብዙ ዉዝግብና ተቃውሞ ያለው ሲሆን የኢህአዴግ መንግስት ከሱዳኖች ጋር በመተባበር በድብቅ ለመከለል ተስማምቷል። እንዲህ ነው የተደረገው፥ በድንበሩ አከባቢ የሚገኙ ኗሪዎች (የኢትዮጵያና የሱዳን) ድንበራቸውን አይተው ክለላውን ይፈፅማሉ፣ ይፈራረማሉ። ለሱዳን የተሰጠው መሬት ታውቋል። ሁሉም ነገር በኢህአዴግና የሱዳን መንግስት አልቋል። አሁን “የሀገር ሽማግሌዎች” እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። የሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈርሙ የተፈለገበት ምክንያት የድንበር ክለላ የተከናወነው በኗሪዎች ነው እንዲባል ነው። ለሌላ ግዜም ምስክር ሁነው እንዲቀርቡ ነው።
በዚህ መሰረት በድንበሩ አከባቢ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ከተሞች ማይካድራና በረከት የተወሰኑ ሰዎች በካድሬዎች ተመርጠው “ኮሚቴ” ተሰኝተው ዛሬ ግንቦት 8, 2006 ዓም እንዲፈርሙ ወደ ሱዳን ድንበር ተጉዘዋል። እነዚህ ኮሚቴ ተብለው የተመረጡ ሰዎች ስለ ድንበሩ ይሁን አከባቢው እውቀት የሌላቸው፣ የአከባቢው ኗሪዎች ሳይሆኑ በቅርብ ግዜ ባከባቢው መሬት የተሰጣቸው ሰፈርተኞች ናቸው። ዕድሜየቸውም ከአርባ በታች ነው፣ ትምህርት የላቸውም፣ የድንበሩ ታሪክ አያውቁም፣ መሬት ስለተሰጣቸውና በካድሬዎች ስለታዘዙ ብቻ ሊፈርሙ የሚችሉ ናቸው። ስለዚህ የሀገር ሽማግሌዎች ሊባሉ አይችሉም። ምክንያቱም ሰፈርተኞች እንጂ ኗሪዎች አይደሉም፣ ወጣቶች ናቸው (ድንበሩ ላያውቁት ይችላሉ)፣ ትምህርት የላቸውም (የድንበር ጉዳይ ምን ያህል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ ላይረዱ ይችላሉ) ወዘተ። ዛሬ እንዲፈርሙ የተወሰዱት በድብቅ መሆኑ ነው።
SUDAN
የድንበር ጉዳይና ሌሎች የሑመራ አከባቢ ኗሪዎች በማየሉ ተቃውሞ እየተቀሰቀሰ በመሆኑ ባከባቢው ተገኝቶ መረጃ ማሰባሰብ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። የመንግስት አካላት ኗሪዎች ለሌሎች አካላት መረጃ እንዳይሰጡ እያስፈራሩ ነው። መረጃ መሰብሰብም አይፈቀድም። በዚሁ አጋጣሚ ግርማይ ወልደግዮርግስ የተባለ የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ባስተዳዳሪዎች ከቀረቡለት አራት ካድሬዎች ዉጭ ሌሎች ኗሪዎችን በማነጋገሩ ምክንያት ባለስልጣናት ፖሊስ ጠርተው አስረውታል። የድምፂ ወያነ ሬድዮ ጋዜጠኛ ህዝብን ሳንፈቅድልህ አገጋግረሃል ተብሎ ነው የታሰረው።
በሑመራ አከባቢ ብዙ ተደራራቢ ችግሮች አሉ። ሕገወጥ የመሬት ሽንሸና እየተደረገ ነው። ኗሪዎችን ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ስርዓቱ ያገለግላሉ ለተባሉ ሰዎች መሬት እየተሰጠ ይገኛል። ለምሳሌ አቶ ካሕሳይ ገብረሚካኤል የተባሉ ያከባቢው ኗሪ መሬታቸው ተወስዶ ለሌላ የህወሓት ካድሬ ዉሽማ ተሰጥቷል። ፍትሐዊ ያልሆነ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
በድንበሩ ጉዳይ በድብቅ እየተፈረመ ያለው ነገር ተቀባይነት የለውም። ለሱዳን የሚሰጥ መሬት መኖር የለበትም። ተግባሩ ሕገወጥ ነው። ኢህአዴግም ለተግባሩ ይጠየቃል።

No comments:

Post a Comment