የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እየሰራ ባለው የዋንኬ መንገድ አካባቢ ከደቡብ ሱዳን የተፈናቀሉ ስደተኞች በሰፈሩ አካባቢ አንድ ሾፌር እና አንድ የልዩ ፖሊስ አባል መገደላቸውን ተከትሎ አካባቢው በፌደራል ፖሊስ መወረሩ ታውቋል፡፡ የግድያው መንስኤ በውል ባይታወቅም የክልሉ ፖሊስ ከኤርትራ ሰርገው የገቡ አሸባሪዎች የፈጸሙት ነው እያለ ነው።
ፉኝዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ደግሞ አንድ ሹፌርና አንድ ማንነቱ በውል ያልታወቀ ባለስልጣን የተገደሉ ሲሆን፣ የገዳዩ ማንነት በውል አይታወቅም። በጋምቤላ ከተማ ደግሞ ከቀናት በፊት በተደረገው የተኩስ ልውውጥ አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ተገድሏል።
ትናንት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ልዩ ሃይል የሚባሉት ታጣቂዎች ደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ ሄደው ሰፍረዋል። ጋምቤላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መረጋጋት አይታይበትም የሚለው ዘጋቢያችን፣ የተኩስ ድምጽም አልፎ አልፎ እየተሰማ መሆኑን ተናግሯል።
በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ክልል እየገቡ መሆኑ ይታወቃል። የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከታሰረ በሁዋላ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱም ይታወቃል። የክልሉን ፖሊስ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት በኔትወርክ ችግር የተነሳ ሊሳካልን አልቻለም።
No comments:
Post a Comment