Saturday, August 10, 2013

Amnesty international asks the Ethiopian Government to stop mass arrest and killing August 9, 2013

መንግስት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና እንዲያቆም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በድጋሚ ጠየቀ! August 9, 2013 ድምፃችን ይሰማ የሰብአዊ መብት ተቋሙ መንግስት ያሰራቸውን ሰላማዊ ዜጎች እንዲፈታና ሰብአዊ መብትን እንዲያከብር አሳስቧል! የትናንት የተሰካ ተቃውሞን ተከትሎ መንግስት የወሰደውን ጸያፍ እርምጃ ተከትሎ አምነስቲ መንግስት የጭቆና ድርጊቱን አንዲያቆም ጠይቋል፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ባወጣው በዚሁ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለው በደል ከልክ እያለፈ መምጣቱን አውስቶ ይህ አይነቱ እርምጃ ድርጅቱን በጣም እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡ ለ18 ወራት የዘለቀውና መንግሰት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆምና ሕገ መንግስቱን እንዲያከብር የሚጠይቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቃውሞ ሰላማዊ ሆኖ መቆየቱ እርግጥ ቢሆንም መንግስት ከፍተኛ እና የማይመጣጠን ኃይል በሙስሊም ሰልፎች ላይ ቢያንስ በአራት የተለያዩ ወቅቶች መጠቀሙን አምነስቲ የጠቆመ ሲሆን በርካታ ሰዎች መሞታቸውና ጥቂት የማይባሉ መቁሰላቸው እዲሁም በርካቶች ለእስር መዳረጋቸውን አውስቷል፡፡Amnesty International ባለፈው ሳምንት በአርሲ ዞን ኮፈሌ የመንግስት ታጣቂዎች በሰላማዊ እና ባልታጠቁ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ እጅግ የከፋ መሆኑን የሚናገረው ይኽው የአምነሲቲ ሪፖርት 14 ያልታጠቁ ሰዎች በታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውን ያትታል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች ሰልፈኞቹ የታጠቁና የሞቱትም ቁጥር ሶስት ብቻ መሆናቸውን ፖሊስም የጉዳቱ ሰለባ መሆኑን ቢገልጹም፤ የመንግስት አካላት ለአምነስቲ ኢንተርናሽል ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውንም ጨምሮ ገልጧል፡፡ በእነነዚህ ግጭቶች ፖሊስ የተጠቀመው ኃይል ያልተመጣጠ በመሆኑም በክስተቱ ላይ ፈጣን እነ ነጻ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ የግጭቱ ውጤት መጣራትና ተጠያቂ የሚሆኑ የጸጥታ ሰራተኞችም ለፍርድ መቅረብ እንደሚኖርባቸውም አሳስቧል፡፡ አምነስቲ በሪፖርቱ መንግስት ከዚህ ቀደም በአርሲ አሳሳና በአማር ክልል ገርባ ከተማ ላይ የወሰደውን አስከፊ የፖሊስ ጥቃት አስታውሷል፡፡ መንግስት ከዚህ በተጨማሪ በአርሲ፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም ቦታዎች ከሰሞኑ ከፍተኛ አፈሳ ሲያካሄድ መክረሙንና ዳርሰማ ሶሪ እና ኻሊድ ሙሐመድ የተባሉ ጋዜጠኞች ጨምረው መታሰራቸውና እስሩም ለ18 ወራት የዘለቀው የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ሰላማዊ ተቃውሞ የታከከ መሆኑን የሚገልጸው የአምነስቲ ሪፖርት ሰላማዊ ሆኖ የዘለቀውን የሙስሊሞች ተቃውሞ መንግሰት አመጸኛና ከአሸባሪነት እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ አድርጎ ደጋግሞ ለመሳል ሲሞክር መቆየቱን፣ ባለፈው ሳምንትም በመንግስት ሚዲያዎች ተከታታይ ሰልፈኞችን ማስፈራሪያ መግለጫ መውጣቱን ገልጿል፡፡ የአምነስቲ ኢንተርናሽል የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተመራማሪ ክሌር ቤስቶን ይህን አስመልክቶ ሲገልጹ ‹‹ይህ የመንግስት መግለጫ ለዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የሰጠውን ህገ መንግስት የሚጥስ ነው›› ይላሉ ጨምረውም ‹‹መንግስት የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ምሬት በኃይል ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት፣ የእቅስቃሴውን መሪዎች ጨምሮ በርካቶችን በማሰር እና ለሽብርተንነት ሰፊ ትርጓሜ በሚሰጠው የአገሪቱ ጸረ ሽብር በመክሰስ ቀጥሏል›› ብሏል፡፡ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰቱ መቀጠሉ እጅግ እደሚያሳስባቸው የሚገልጹት ተመራማሪው ዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ለእስር እንግልት ከመጋለጣቸውም በላይ ይህ ሁኔታ ለተጨማሪ ደም መፋሰስ ሊያመራ እንደሚችል ይሰጋሉ፡፡ ደርጅቱ መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት እንዲያከብርና ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንዲገታ እዲሁም እነዚህ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን የተጠቀሙ ዜጎች በአስቸኳይ አንዲፈቱም አምነስቲ በመግለጫው አሳስቧል፡፡ መግለጫው የሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞን መነሻዎችም በስፋት አብራርቷል፡፡

No comments:

Post a Comment