Tuesday, January 13, 2015

ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድ በሁለት ሳምንት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ውሳኔ አስተላለፈ


election board
ምርጫ ቦርድ በታዛቢነት በጉባኤው አልተገኘምበጥቅምቱ ጠቅላላ ጉባኤ በመልቀቂያ የተሰናበቱት አቶ አበባው መሃሪ ጥሪ ቢደረግላቸውም አልተገኙም ለአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛ እና የጀርመን ሬድዮ የዐማርኛ ድምፅ ዘጋቢዎች ጥሪ ቢደረግም አልተገኙም 425 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተገኝተዋል፡፡
መኢአድ በሁለት ወራት ውስጥ ሁለተኛውን የተሳካ ጠቅላላ ጉባኤውን ጥር 3/2007 ዓ.ም አካሄደ፡፡ጉባኤው ከመላው ሀገሪቱ በተሰበሰቡ ቁጥራቸው 425 በሚሆኑ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በተገኙበት የተካሄደው ምርጫ ቦርድ ከጥቅምት 28-30/02/2007 መኢአድ ያደረገውን የተሟላ ጠቅላላ ጉባኤ አልተቀበልኩትም በማለቱ ምክንያት ነው፡፡ምርጫ ቦርድ የመኢአድን የጥቅምቱን ጉባኤ አለቀበልም ያለበት ምክንያት ተከትሎ ዛሬ በተደረገው ሁለተኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ምርጫ ቦርድ በታዛቢነት እንዲገኝ ቢጋበዝም አልተገኘም ፡፡ ለምን አንዳልተገኝ ምክንያቱ ባይታወቅም ከመኢአድ ለምርጫ ቦርድ በታዛቢነት እንዲገኘ ጥሪ የደረገለት መሆኑ እና መልክቱም በፖስታ ቤት እና በስልክ እንዳነጋገሯቸው ተረጋግጧል፡፡ የጠቀሱት የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አቶ ተስፋየ መላኩ ጠቅላላ ጉባኤው መጀመር ከነበረበት ጊዜ 30 ደቂቃ ዘግይተው የመክፈቻ ንግግር በማድረግ የእለቱን ጉባኤ አስጀመሩ፡፡ አያይዘውም ጉባኤው ዘግይቶ ሊጀመር የቻለው ከምርጫ ቦርድ ተወካይ እስኪመጣ እየተጠበቅ መሆኑን እና አሁን በስልክ በተነገራቸው መዕልክት ምርጫ ቦርድ የጥር 3/2007 ዓ.ም ጉባኤ የሚካሄደውን የመኢአድን ጉባኤ ለመታዘብ ፈቃደኛ አለመሆኑን ለጉባኤው ነግረው መድረኩን ለመኢአድ ፕሬዘዳንት ለአቶ ማሙሸት አማረ አስረከቡ፡፡አቶ ማሙሸት አማረ ወደ መድረክ ሲወጡ በከፍተኛ ጩህትና ጭብጨባ ጉባኤው ተቀበላቸው፡፡እርሳችም ከመድረክ ለተደረገላቸውን የክብር አቀባበል አመስግነው መኢአድ የሚደረግበትን የፖለቲካ ሴራና ደባ ተረድታችሁ በአስቸኳይ ና ድንገተኛ ጥሪ ከአራቱም የሐገሪቱ ማዕዘናት ለተሰበሰባችሁ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የከበረ ምስጋና ይገባችኋል በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡
ዋና አጀንዳቸውን ለቤቱ ያስተዋወቁት በሚከተለው የመግቢያ መዕልክታቸው ነው፤ መኢአድ በመመሪያው መሰረት እና በጠቅላላ ጉባኤ አባለት ጥያቄ የውስጥ ችግሩን በእርቅ ለመፍታታት ጥቅት 28/02/07 የላዕላይ ም/ቤቱ እና ጥቅምት 29-30/02/07 ዓ.ም አስቸኳ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄዷል፡፡
በጉባኤውም ፤ሁሉም የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተገኘተዋል፤ ዋና አጀንዳ የነበረው ውስጥ ችግሩን መፍታት ነበር ፤ የጉባኤው ውሳኔም የመኢአድን የወደፊት የስራ አመራር እቅድ ማጽደቅ እና ትክክለኛ የመኢአድ አመራር አባላትን መምረጥ ነበር፤በዚህ ጉባኤ ላይ ሁለት የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ተገኝተው ነበር፡፡ታዛቢዎቹም ምዕላተ ጉባኤውን ቆጥረው የቃለ-ጉባኤ ስነ-ሥርዓቱን አረጋግጠው ጉባአው ሊጀመር እንደቻለ አቶ ማሙሸት አስታውሰዋል፡፡ ጉባኤውም የአመራሩን የውስጥ ችግር ጥቅምት 28 አይቶ በ29/02/07 ለሚካሄደው የጠቅላላ ጉባኤ መርቶት ነበር፡፡ይህንንም የጉባኤ ውሳኔ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች ታዝበዋል፡፡የውስጥ ችግሩም በጠቅላላ ጉባኤው በሰላማዊ መንገድ መፈታቱን የቦርዱ ታዛቢዎች ተመልክተዋል፡፡
ሁኖም ግን የመኢአድ የውስጥ ችግር አፈታት ሂደት ምንም ዓይነት የሕግም ሆነ የአሰራር ክፍተት እንደሌለበት እየታወቀ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ያስተላለፈው መኢአድን የተመለከተው መግለጫ ከህግ እና ከአሰራር ያፈነገጠ ፍፁም ወገንተኝነትን የተከተለ በመኢአድ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የገባ ነው ብለዋል፡፡ ሁኖም ሰላማዊ ትግል ብዙ እልህ አስጨራሽ በመሆኑ ምርጫ ቦርድ የሚፈጽመውን የፖለቲካ ደባና ሴራ ለህዝባችን ማጋለጥ ተገቢ በመሆኑ የመኢአድ የጠቅላላ ጉባኤ አባለት በሁለት ወራት ውስጥ ብዙ መስዋትነት ከፍለው ለጥር 3/2007 አስቸኳይ ጉባኤ መገኘት በመቻላቸው አድንቀው አሁንም በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ ቦርድ ያልተገኘው አንጋፈውን ድርጅት መኢአድን ከምርጫ ለማስወጣት በሚደረግ ሴራ ውስጥ ስለሆነ ሊሆን አንደሚችል በማሳወቅ መኢአድ ከግንቱ 2007 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ እና በተለያዩ አካለት ፖለቲካዊ ውሳኔ ቢወጣ ሊከተል ስለሚችለው የትግል ስልት ወደፊት ቆም ብሎ ሊያስብ ይገደዳል በማለት አስረግጠው የተናገሩት የድርጅቱ ፕሬዘዳንት ከጠቅላላ ጉባኤው አባለት የማያባራ ድጋፍና ጭብጫባ ያጅባቸው ነበር፡፡
በመቀጠል ምርጫ ቦርድ የጥቅምቱን ጉባኤ እና የአመራር ምርጫ በራሱ ታዛቢዎች ተወክሎ ተከታትሎ አሁን ድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ እስከ ጥር 4 ድረስ ያሳውቀኝ ባለው መሰረት ጉባኤው ይህንን ተረድቶ ሁለት ውሳኔዎችን ተወያይቶ እንዲወስን አሳሰቡ፡፡
ሁለቱ የዕለቱ ዋና ዋና አጀንዳዎችም ፤ባለፈው ጥቅምት 28-30/2007 የተደረገውን የመኢአድ አመራር እንደለ በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ማስቀጠልአ፤ወይም በዛሬው ጉባኤ አዳዳስ አመራር አባላትን መምረጥ የሚሉ ነበር ፡፡ በሁለቱም ሀሳቦች ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው የጥቅምቱን የጠቅላላ ጉባኤ የአመራር ምርጫ እንዳለ ማሰቀጠል የሚለውን ሀሳብ በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ አፅዲቋል፡፡ በዚህም መሰረት
1-አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድ ፕሬዘዳነት
2-ዶ/ር ታደወስ ቦጋለ የመኢአድ ተ/ም/ፕ/ት
3-አቶ እንዲሪያስ ኢሮ የመኢአድ ም/ፕ/ት
4-አቶ ተስፋየ መላኩ የመኢአድ ዋና ፀሀፊ ሁነው ይቀጥላሉ፡፡
በማንኛውም መንገድ የመኢአድን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ሊለውጠው ወይም ሊሽረው የሚችለው የመኢአድ ጠቅላላ ጉባኤ ብቻ ነው፡፡አቶ አበባው መሃሪ ፀረ-መኢአድ አስተሳሰብ ካላቸው ቡድኖች ጋር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በታሪክ ይቅር የማይባል የባንዳነት ተግባር በመሆኑ በአስቸኳይ ጉዳዩን የሚከታተል ቡድን እንዲቋቋም ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል፡፡ጠቅላላ ጉባኤው ባለ አስራ አንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ በመጨረሻም በጠቅላላ ጉባኤው በህግና በስነ-ስረዓት ከሚመራው በኢአድ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴወች ፈፅሞ ተቀባይነት የሌላቸው ሲሆኑ በውጭም በአገር ውስጥ ያሉ የሚዲያ ተቋማት ይሕንን በመገንዘብ ብዙ መስዋትነት የተከፈለበትን አንጋፋውን ድርጅት ለማፈራረስ የተላላኪነት አጀንዳ አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር የሚያደርጉት ማንኛውም የመረጃ ልውውጥ መኢአድን አይወክልም ብለዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ * (ወይዘሪት ወይንሸት )ከፍተኛ ድብደባ ተፈፀመባት ...

January 13,2014

የአንድነት ፓርቲ ሴቶች ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ከፍተኛ ድብደባ  ተፈፀመባት ወይዘሪት ወይንሸት፣ ንፍስ ስልክ አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ ሁለት ሰዎች ከረፋዱ 5፡30 ላይ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባት ለፍኖተ-ነፃነት የደረሰው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወይዘሪት ወይንሸት፣ ነፍሰጡር መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን ደብዳቢዎቹም ሆዷን በመርገጥ ድብደባውን ሲፈፅሙባት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ደብዳቢዎቹ ድብደባውን ፈፅመው የተሰወሩ ሲሆን ወይዘሪት ወይንሸት፣ በአሁኑ ሰዓት ራሷን ስታ ሆስፒታል መግባቷን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወይንሸት፣ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በከፍተኛ ድምፅ የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆና በመመረጥ በምርጫው ላይ ጉልህ ሚና በመጫወት ድርሻዋን መወጣቷ ይታወሳል፡፡ በእለቱ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአንድነት ስም የሚነግዱትን ግለሰቦች በማውገዝ አስተያየቷን መሰንዘሯን ተከትሎ ድብደባው ሊፈፀምባት እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወይዘሪት ወይንሸት፣ በፓርቲው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያላት ወጣት ከመሆኗም በተጨማሪ የአንድነት ፓርቲ ሴቶች ጉዳይ ምክትል ሀላፊ በመሆን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ሳምንት ብቻ በአንድነት አባላት ላይ ድብደባ ሲደርስ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፈው እሁድ በአቶ መሳይ ትኩ፣ ላይ ድብደባ መፈፀሙ ይታወሳል፡፡

ትናንት ከዉጭ ወራሪዎች የታደገን መከላከያ ሠራዊታችን ዛሬም ከአገር ዉስጥ ወራሪዎች ይታደገናል


አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ እድገቱን ለሚመኙ አስተዋይ መሪዎች እለታደለምና ደሃ ነዉ፤ ረሀብተኛ ነዉ አልተማረም ወይም ኋላ ቀር ህዝብ ነዉ ማለት ይቻል ይሆናል፤ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ያሰኘዉን ያክል ቢደኸይ ወይም ኋላ ቀር ቢሆን ለነፃነቱ፤ ለአንድነቱና ለግዛት አንድነቱ መከበር ያለስስት ደሙን የሚያፈስ ጀግና ህዝብ ነዉ። ይህ ጀግንነት ደግሞ አንደተረት በአፍ ተነግሮ የሚያበቃ ሳይሆን በመተማ፤ በአድዋ፤ በማይጮዉ፤ በወልወል፤ በፊልቱና በጎዴ የጦር ሜዳዎች ሊወጉትና ሊወሩት የመጡ ጠላቶቹ ጭምር የመሰክሩለት የታሪክ ሐቅ ነዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከጀግንነቱ ጋር አርቆ አስተዋይና ታጋሽ ህዝብ ነዉ፤ ሆኖም ይህንን ህዝብ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በተከታታይ የገዙት የገዢ መደቦች ጀግንነቱን ለራሳቸዉ ክብርና ዝና ታጋሽነቱን ደግሞ ለስልጣን ዘመናቸዉ ማራዘሚያ አድርገዉ የመከራ ዘመን እያስቆጠሩ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ታጋሽ ህዝብ ቢሆንም እርግጫዉና ጭቆናዉ በበዛበት ቁጥር አምርሮ የሚነሳ ለገዢ መደቦች የማይመች ቁጡና እልህኸኛ ህዝብ መሆኑንም በተከታታይ አሳይቷል። ይህንን ደግሞ በ1966 ዓም ከዳር ዳር ባቀጣጠለዉ ህዝባዊ አብዮት በ1983 ዓም ደግሞ በአራቱም ማዕዘናት ባካሄደዉ ህዝባዊ አመጽ አሳይቷል። ሆኖም አብዮቱንና ህዝባዊ አመጹን ከትግል ሜዳ እስከ ፖለቲካ ስልጣን አደባባዮች ድረስ አቀነባብሮ የሚመራ የተደራጀ ህዝባዊ ኃይል ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ህዝብ የታገለላቸዉ የትግል ዉጤቶች ሁሉ የአምባገነኖች መጠቀሚያ ሆነዉ ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግና ነዉ፤ ተጋሽ ነዉ፤ ወይም አርቆ አስተዋይ ነዉ ሲባል እንዚህ እሴቶች ወንዱን፤ ሴቱን፤ ምሁሩን፤ ገበሬዉን፤ ሰራተኛዉንና መለዮ ለባሹን ሁሉ የሚያጠቃልሉ ህዝባዊ እሴቶች ናቸዉ እንጂ የአንድ ህብረተሰብ ክፍል ልዩ ንብረቶች አይደሉም። በእርግጥም አብዛኛዉ የታሪካችን ክፍል በአገር አንድነት ግንባታና ይህንኑ አንድነት ከዉጭ ወራሪዎች በመከላከል ጦርነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ ጀግንነትን በቀጥታ የምናያይዘዉ ከዚሁ አገርንና የአገር አንድነትን ከማስከበር ስራ ጋር ነዉ። በእርግጥ አገርን ከጠላት መከላከል ጀግንነት ነዉ፤ ሆኖም መሳሪያ ተሸክሞ አገሩን ከጠላት የሚከላከል ሠራዊት ምን እለብሳለሁ፤ ምን እበላለሁ፤ በምንስ እዋጋለሁ ከሚለዉ ስጋት ተላቅቆ በሙሉ ኃይሉና አዕምሮዉ መዋጋት የሚችለዉ እንደነሱ ጀግና የሆነና በደጀንነት የተሰለፈ ህዝብ ሲኖር ብቻ ነዉ።
እስከ አድዋ ጦርነት ድረስ አገራችን ኢትዮጵያ የመሪዉን የክተት አዋጅ ጥሪ እየሰማ የሚዘምት ህዝብ እንጂ ቋሚ የመከላከያ ሠራዊት አልነበራትም። ባለፉት 60 አመታት ግን ኢትዮጵያ የምድር ጦር፤ አየር ኃይል፤ ብሔራዊ ጦርና እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ደግሞ የባሕር ኃይልን ጭምር ያካተተ ዘመናዊ የመከላከያ ሠራዊት ነበራት። ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ስልጣን እስከጨበጠበት እስከ 1983 ዓም ድረስ የነበረዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሞላ ጎደል በመስኩ ልምድ፤ ችሎታና እዉቀት ባካበቱ ባለሙያዎች የተሞላና የአገረን ዳር ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር ለወገናቸዉ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ደህንነት ቀና አመለካከት ባላቸዉ አገር ወዳዶች የተገነባ ሠራዊት ነበር። ወያኔ በ1983 ዓም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህንን አገር ወዳድ የሆነ ፕሮፌሺናል ሠራዊት በትኖ ነዉ ለአንድ ድርጅት ጥቅምና ዝና በቆሙ፤ ፊደል ባልቆጠሩና ሙያዊ ብቃት በሌላቸዉ መሀይሞች የተሞላ መከላከያ ሠራዊት የተካዉ። እንደዚህ ስንል ግን ወያኔ በገነባዉ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዉስጥ አገራቸዉ ኢትዮጵያን ከራሳቸዉ በላይ የሚወዱና ለአገራቸዉና ለወገናቸዉ ክብርና ጥቅም መስዋዕት ለመሆን የቆረጡ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፤ እንዲያዉም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚመራዉና የግዳጅ ትዕዛዝ የሚወስደዉ አገራቸዉን በሚጠሉ ዘረኞች መሆኑ ነዉ እንጂ ዛሬም ቢሆን አብዛኛዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል የእናት አገሩ ዳር ድንበር መደፈርና የወገኖቹ መረገጥ የሚያንገበግበዉ አገር ወዳድ ሠራዊት ነዉ።
የ1966ቱ ህዝባዊ አብዮት ሲፈነዳ የነበረዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፊዉዳሉ መንግስት የደሞዝ ጭማሪ አድርጎለት ከህዝባዊ ኃላፊነቱ ሊያዘናጋዉ ሲሞክር – “ሎሚ ተራ ተራ፤ “ሎሚ ተራ ተራ እኛስ አግኝተናል ሲቪሉን አደራ” ብሎ የህዝብ ወዳጅነቱን ያረጋገጠ አገር ወዳድ ሠራዊት ነበር። አመጸኛዉ ደርግ ይህንን ሠራዊት ተጠቅሞ ነዉ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን ስርዐት ያስወገደዉና የመሬት አዋጅን የመሳሰሉ ስር ነቀል አርምጃዊዎች መዉሰድ የጀመረዉ። አምባገነኑ ደርግ ቁልፍ በሆኑ የመከላከያ ሠራዊት ተቋሞች ዉስጥ ታማኝ የሆኑ የራሱን ሰዎች አስቀምጦ ለ17 አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ቢረግጥም ጄኔራል ተፈሪ በንቲን፤ ኮሎኔል አጥናፉ አባተን፤ ተስፋዬ ትርፌን፤ ጄኔራል መርዕድ ንጉሴን፤ ቁምላቸዉ ደጄኔን፤ አምሀ ደስታንና ፋንታ በላይን የመሳሰሉ እስከመጨረሻዉ ትንፋሻቸዉ ድረስ ህዝባዊ አደራቸዉን የጠበቁ ታማኝ የህዝብ አገልጋዮች በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ነበሩ። በንጉሰ ነገስቱም ዘመን ቢሆን ገና ከጥዋቱ ከዝናና ጥቅም ይልቅ የአገራቸዉን ጥቅም ያሰቀደሙ እንደ ጀኔራል መንግስቱ ነዋይ አይነት የለዉጥ አርበኞች ነበሩ።
ወላድ በድባብ ትሂድ – ዛሬም ቢሆን እጅግ በጣም ጨለማ በሆነዉ ጨካኝና ዘረኛ ስርዐት ዉስጥ ጨለማዉን እየገለጡ በድፍረት የአገራቸዉን ህዝብ ጩኸትና ሰቀቃ አዳምጠዉ ዘረኝነት በቃ ያሉ ጀግኖች በመከላከያ ሠራዊቱ ዉስጥ አሉ። በአንድ ቋንቋና በዘር ሰንሰለት ተሳስረዉ የሚሰሩ የወያኔ ደህንነቶች መግቢያዉንና መዉጪያዉን ቆልፈዉ ለጌቶቻቸዉ ዘብ ቢቆሙም ጀግናና ጭስ መዉጪያ አያጣምና ከፍተኛ ልምድና ችሎታ ያላቸዉ የወያኔ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከወያኔ ጎራ እየወጡ የህዝባዊ አመጹን ጎራ እየተቀላቀሉ ነዉ። ሁላችንም በየቀኑ በግልጽ እንደምናዉ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁለት አይነት ዜግነት ፈጥረዋል። አንደኛዉ ዜግነት ወያኔና አገራቸዉን ከድተዉ የወያኔ ተላላኪ በሆኑ እንደነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ፤ አዲሱ ለገሰና ሬድዋን ሁሴንን በመሳሰሉ ሆድ አደሮች የተሞላ ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ዜግነት ደግሞ አገር ወዳዶችና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ያሉበት ነዉ። ከእንደዚህ አይነቱ በዘር ከተከፋፈለና እያንዳንዷ ኮሽ ያለች ነገር በወያኔ ደህንነት ሰራተኞች ተመዝግባ በምትመረመርበት አገር ዉስጥ ለህዝባዊ አላማ ጸንቶ መቆምና ስርዐቱን አልፈልግም ብሎ የነፃነት ኃይሎችን መቀላቀል ከፍተኛ ጀግንነትንና ቆራትነትን ይጠይቃል። ቆየት ባለዉ ግዜ እነ መቶ አለቃ ተሾመ ተንኮሉና ጄኔራል ከማል ገልቹ፤ አሁን በቅርቡ ደግሞ ሦስቱ የተዋጊ ሂሊኮፕተር አብራሪዎችና አራቱ ባለከፍተኛ ማዕረግ የአየር ኃይል ተዋጊ ጄት አብራሪዎች የወሰዱት ህዝባዊ እርምጃ ከሆነ በኋላ በሰበር ዜና ስንሰማዉ ቀላል ይመስላል እንጂ እርምጃዉ ጀግንነትን፤ ቆራጥነትንና በህይወት መወራረድን ይጠይቃል። እነዚህ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለእኩልነት የቆሙ ቆራጥ ዜጎች በወሰዱት እርምጃ አገር ዉስጥና ከአገሩ ዉጭ የሚኖረዉን ኢትዮጵያዊ እጅግ በጣም ደስ አሰኝቷል። በእርግጥም እነዚህ ጀግኖች የወሰዱት እርምጃ ህዝባዊ ትግሉን የሚያነቃቃና የሚያጠናክር ነዉና በልጆቻችን እርምጃ ልንኮራና ደስ ሊለን ይገባል። ሆኖም ይህ ቆራጥ እርምጃ የትግል ጥሪም ነዉና ሁላችንም ጥሪዉን አዳምጠን ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ አቤት ማለት አለብን።
ዛሬ ለአመታት በላይ ሲታመስና ሲብሰለሰል የቆየዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት ገንፍሎ ወጥቶ ወደ ለየለት ህዝባዊ አመጽነት እየተቀየረ ነዉ። ይህንን ህዝባዊ አመጽ በትክክል መርቶ ከግቡ ለማድረስና ከዚህ በፊት በተከታታይ የተፈጠሩትን የስልጣን ከፍተቶችና ስህተቶች አርሞ ትግሉን በእስማማኝ መሰረት ላይ ለማቆም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ታሪካዊና አገራዊ ሃላፊነት አለበት። በቅርቡ ተዋጊ የጦር ሂሊከፕተራቸዉን እንደያዙ የወያኔ ስርዐት በቃን ብለዉ የነጻነት ሀይሎችን የተቀላቀሉት ጀግኖች ዜና ሲሰማ ወያኔ ከፍሎ ያሰማራቸዉ ተናካሽ ዉሾቹ ያንን የለመዱትንና የተካኑበትን እንቆርጣችኋለን እንፈልጣችኋለን የሚል ተራ ዛቻቸዉን አሰምተዉናል። ከዚህ አልፈዉም ወያኔ የታጠቀዉን መሳሪያ ዘመናዊነትና ያደራጀዉን ሠራዊት ብዛት ደጋግመዉ በመጥቀስ እነሱን መንካት ከእሳት ጋር መጫወት እንደሆነ ሊነግሩን ሞክረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ በወቅቱ ስሙን እንኳን አጣርቶ የማይጠራዉ ህወሓት ከሰሃራ በታች ተወዳዳሪ የለዉም የተባለዉ ሠራዊት የገነባ ኃይል ለምን አንደሚዋጋ እንኳን በማያዉቅ ጀሌ ጦር ማሸነፍ ከቻለ ዛሬማ ፍጹም የሆነ ህዝባዊ መሠረት ያላቸዉና ለምንና ለማን እንደሚዋጉ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ የነጻነት ኃይሎች ካሰቡበት ለመድረስ የሚያግዳቸዉ ምንም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ወያኔና ሆድ አደር ደጋፊዎቹ ተንቅቀዉ ሊያዉቁ ይገባል። ወያኔ ልቡ ስላበጠ የተለቀ ይምሰለዉ እንጁ የትልቅነቱ መገለጫ አድርጎ የሚተማመንበት የመከላከያ ሠራዊት ያቺ የፍጥጫ ቀን ስትመጣ ወያኔን ለመደምሰስ ወገኖቹን የሚቀላቀል ሠራዊት ነዉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት የወሰዱት ህዝባዊ እርምጃም በአየር ኃይሉ ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን ቀን፤ ግዜና ሁኔታ እየመረጠ እግረኛ ሠራዊቱም የሚወስደዉ እርምጃ እንደሆነ ያለ ጥርጥር እናምናለን።
ዉድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሆይ – አንተንና ወገኖችህን በዘር ከፋፍሎ እየገዛ አገርህን የሚያፈርሰዉ ወያኔ ለዚህ እኩይ ስራዉ የሚጠቀመዉ አንተኑ ከህዝብ አብራክ የወጣኸዉን የህዝብ ልጅ ነዉ። በቅርቡ ባህር ዳር ዉስጥ የቅዱስ ታቦት ማደሪያ የሆነዉን ቦታ ከቤ/ ክርሲቲያን ቀምቶ የሸቀጥ መሸጫ ለማድረግ ያደረገዉን ሙከራ የተቃወሙ ኢትዮጵያዉያን ወንድሞችህና ወንድሞችህ እንዲሁም አለም በቃኝ ያሉ መነኩሴ ጭምር በጥይት ጨፍጭፏል። በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር ቆርጦ ትግራይ ላይ የቀጠለዉ ወያኔ ይህ ፀረ ህዝብና ፀረ አገር ወንጀል አልበቃ ብሎት ለዘመናት አብሮ የኖረዉን የትግራይንና የጎንደርን ህዝብ ለማባላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነዉ። በታህሳስ ወር አጋማሽ ጎንደር ዉስጥ የትግራይና ክልልና የጎንደር ሚሊሺያዎች የተኩስ ልዉዉጥ ካደረጉ በኋላ ወያኔ አገርን ለመዉረር በሚመጣ ጠላት ላይ እንጂ በራሱ ወገን ላይ መዝመት የሌለባቸዉን ከ30 በላይ ታንኮችና ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ጎንደር በማሰማራት አገሩንና ወገኑን መጠበቅ ያለበትን ሠራዊት ከገዛ ወገኖቹ ጋር እንዲፋጠጥ አድርገዋል።
በዚህ ፈታኝና እጅግ በጣም አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሂድና ግድል በተባለ ቁጥር መጠበቅና መንከባከብ የሚገባዉን የገዛ ወገኖቹን የማይገድል አስተዋይና ወገንተኛ ሠራዊት መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት። አዎ! የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምንግዜም ቢሆን በአገሩ ጠላቶችና ወራሪዎች ላይ ብቻ እንጂ እያበለና እያጠጣ ባሳደገዉና እኔንና አገሬን ጠብቅ ብሎ ባስታጠቀዉ ህዝብ ላይ በምንም አይነት አፈሙዙን አያዞርም። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ በላይ ጠላት የላቸዉም። ህዝብና አገር እስከ ምድር ፍጻሜ ድረስ አብረዉ የሚዘልቁ ተከታታይ ክስተቶች ናቸዉ፤ ወያኔ ግን ትናንት በጠመንጃ ሀይል መጥቶብን እኛንና አገራችንን ለማጥፋት የሚታገል የለየለት ጠላት ነዉ። ከዛሬ ጀምሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ወያኔን ከዉስጥ ሆኖ መቦርቦር አለበት፡ ይህንን ማድርግ ካልቻለ ደግሞ ወያኔ ከወገኖቹ ጋር እንዲዋጋ ሲያሰማራዉ ወያኔን እየከዳ ከነጻነት ኃይሎች ጋር ተቀላቅሎ ወያኔን ለመደምሰስ በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ ወሳኙን ሚና መጫወት ይኖርበታል። ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህ ቀደም እንዳደረገዉ ሁሉ አሁንም እንደገና ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት . . . ና ተቀላቀለንና አንድ ላይ ሆነን ወያኔንና ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት ቀብረን የኢትዮጵያን ህዝብ ከዉርደት፤ ከእስር፤ ከድብደባ ከግድያና ከስደት እናድን የሚል አገራዊ ጥሪዉን ከአደራ ጋር ያስተላልፋል።

Monday, January 12, 2015

የአርቲስት አስቴር በዳኔና ሳሞራ ፍጥጫ በደደቢት በረሃ


Aster Bedae
…አርቲስት አስቴር በዳኔ ከተቀመጠችበት ወደፊት ወጥታ ማይኩን ስትጨብጥ ፍርኃት ቢጤ እንደወረራት ከመጀመሪያው ያስታውቃል፡፡ ‹‹በጣም ነው የሚያስፈራው፤›› በማለት የጀመረችውን አስተያየቷን የያዘችውን ማስታወሻ እያነበበች አስተያየት መስጠት ቀጠለች፡፡
‹‹ይህንን ዕድል ተመቻችቶልን በቴሌቪዥን ስናየው የኖርነው ታሪክ ለማየት ስለቻለን እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በፊት የነበረኝ ያልተጨበጠ አመለካከት በመረጃ የተደገፈ ሆኗል፤›› በማለት ሐሳቧን ቀጠለች፡፡ ‹‹እውነትን መናገር እወዳለሁ፡፡ የሐሳብ ነፃነትም አለ፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ ያሰኘች ሲሆን፣ በሒደትም የፍርኃቷ መጠን እየቀነስ የመጣ ይመስላል፡፡
አርቲስት አስቴር በዳኔ
‹‹ዛሬ ባልናገረው የሚቆጨኝ የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ በጣም ከባድ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በጆሮ ስሰማው ደርግ ተደምስሶ ታጋይ እንዲህ ሆኖ ሲባል ከሁለቱም ወገን የተሰዉት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ የሞቱት፣ እግራቸው የተቆረጠ፣ ዓይናቸው የጠፋ ስላሉ ለሁለቱም ‹ጠላት› የሚለው ቃል ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የወንድማማቾች ደም በመፍሰሱ ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ሄደን ስናይ ልብ የሚሰብር ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የጦርነትና የትግል ታሪክ ዘመኑ የፈጠረው ነው፡፡ በወቅቱ መንግሥታዊ ለውጥ ለማምጣት የትጥቅ ትግሉ አማራጭ አልነበረውም፡፡ አሁንስ?›› አርቲስት አስቴር ትንፋሿን ዋጥ በማድረግ ቀጠለች፡፡
‹‹የትግሉ ዋና ሐሳብ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ ለማምጣት ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የሥርዓት ለውጥ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ እንዲሆን ነበር ያ ሁሉ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለው፡፡ አሁን ላይ ሲታሰብ የሚመጣው ግንቦት ላይ 24 ዓመት የሚሆነው ሥልጣን ላይ ያለው አንድ ፓርቲ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ላይ ልባችሁ ምን ይላል? ያኔ ለሥልጣን ሳይሆን ለሕዝብ ስትታገሉ በጦርነት ሳይሆን በዲሞክራሲ ለውጥ እንዲደረግ ነበር፡፡ አይለደም?›› በማለት ጠየቀች፡፡
‹‹በእርግጥ የድሮን አስተሳሰብ መናፈቅ አዲስ አስተሳሰብ ለመቀበል ይከብዳል፡፡ አሁን ዝም ብዬ ሳስበው ራሱ ተቃዋሚ የሚለው ቃል ራሱ ጥሩ አይደለም፡፡ ተፎካካሪ ቢባል፡፡ አዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ያለው ተተኪ መሪ ሊፈጠር አይችልም የሚል አቋም ነው ያላችሁ?›› በማለት ሐሳቧን ያልቋጨችው አርቲስት አስቴር፣ ሐሳቧ በብዙዎች ተጠብቆ የነበረ አይመስልም፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› የሚለው የመጨረሻውን ቃል እስክትናገር ከአጠገቧ የተቀመጡ ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት አንጋፋ ታጋዮች ጥያቄው እስኪያልቅ የተጨነቁ ይመስላል፡፡ እርስ በርስ አየት ተደራርገው የተለዋወጡት ፈገግታ ጥያቄውን የጠበቁት እንዳልሆነ ያሳብቃል፡፡ በእርግጥም በምርጫ ዋዜማ ሆነው ለጥያቄው ምን ተብሎ ምላሽ እንደሚሰጥ ሳያስጨንቃቸው አልቀረም፡፡
‹‹እውነት መናገር እውዳለሁ›› በሚል የጀመረችው ፍርኃት እየፈጠረባትም ቢመስል የመጨረሻ ማጠናቀቂያ ሐሳቧ እንዲህ ነበር የሚለው፡፡ ‹‹ምክንያቱም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፡፡ ‘So, next time’ ምን ያህል አዲስ ታሪክ አዲስ አስተሳሰብ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተለውጦ እናያለን?›› የሚለው ፈራ ተባ እያለች የጨረሰችውን ጥያቄ ‹‹ውርድ ከራሴ›› ይመስል ድምጿ እየተቆራረጠ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብላ፣ ‹‹እናንተስ በምርጫ ትወርዱ ይሆን?›› ብላ ነበር ጥያቄዋን የቋጨችው፡፡
አቶ በረከት ስምኦን ሁለት እጆቻቸውን ወደፊት ወስደው እንደማፍተልተል ሲያደርጉ፣ ሌሎች ብዙዎቹ አንጋፋ አመራሮች በግርምት ጉንጫቸውን ደገፍ አድርገው ይዘው ቀታይተዋል፡፡

ታሪካዊው ጣይቱ ሆተል ተቃጠለ:

- በውስጥ እና በውጭ የተከሰተበትን የፖለቲካ ውጥረት አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነው::
- ጣይቱ ሆቴል ስዬ አብርሃ ለቅርብ ዘመዳቸው ለሆኑት አቶ ፍፁም ዘአብ ሽጠዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዘመናዊ ሆቴል የሆነውና ለሀገሪቱ እና ለሕዝቡ እንደ ታላቅ ቅርስ የሚታየው ጣይቱ ሆቴል ተቃጠለ። በቦታው የነበሩ የዓይን ምስክሮች እንዳሉት ሆቴሉ መሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ በእሳት ጋይቷል።
በሃገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ወያኔ በምርጫው ጉዳይ እና በተለያዩ የምእራባውያን ጫና የተወጠሩት በህዝብ ጥያቄ የተጨነቁት የወያኔ ባለስልጣናት የህዝቡን የአስተሳሰብ አቅጣጫ ለማስቀየር እና ሃሳብ ለመስረቅ ለማስደንገጥ እና አዲስ መወያያ ጉዳይ ለመፍጠር ያደረገው ተንኮል ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ::
ከ 75% በላይ በእሳት የጋየው ጣይቱ ሆቴል እሳቱ የጀመረው ከማለዳው 2 ሰአት ቢሆንም እሳት አደጋ መኪኖች የደረሱት ግን 3.30 ሰአት ነው። ሆቴሉ አቶ ስዬ አብርሃ የፕራይቬታይዜሽን ሀላፊ በነበሩበት ወቅት ጣይቱ ሆቴልን እና ጉለሌ ሳሙና ፋብሪካን ለቅርብ ዘመዳቸው ለሆኑት አቶ ፍፁም ዘአብ ሽጠዋል።
በ 1993 ሕወሃት ለሁለት ተሰንጥቆ አቶ ስዬ የሙስና ክስ ሲመሰረትባቸው የጣይቱ ሆቴል ጉዳይ በክሱ ላይ ተመልክቷል። የሆቴሉ ባለቤትም አቶ ፍፁም ለበርካታ አመታት በእስር መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ ፍፁም ዘአብ በሂደት ላይ ባለው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የሙስና መዝገብ ታስረው የነበረው ሲሆን አቃቢ ህግ በቂ ክስ አላቀረበባቸውም በማለት በነፃ ተሰናብተዋል።
ፒያሳ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ባካባቢው የደረሱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ቅድምያ ገንዘብ በመጠየቃቸውና በሚከፈላቸው ገንዘብ መጠን ዙሪያ በፍጥነት ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው እሳቱ ጌዜ አግኝቶ ሊስፋፋ ችሏል።
አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ እንዲህ በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል፣
“ፒያሳ ጣይቱ አከባቢ እያተቃጠለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው:: የእሳት አደጋ መኪና በቦታው ቢቆምም ውሃ የሚረጩት ከህዝቡ ጋር ሳንቲም እየተደራደሩ ባለበት ሁኔታ ንብረት እየተንቦለቦለ ነው:: ካጠፉት ብኋላ ገንዘብ ቢጠይቁ ምን ችግር አለው?”
ሌላኛው ወጣት ደግሞ እንዲህ ብሏል፣
“ልብ የሚሰብር ዜና - ጣይቱ ሆቴል እየተቃጠለ ነው። በአካባቢው ያለነው ወጣቶች ቀርበን እንዳናጠፋ ፓሊስ እያገደ ነው።”
አሁንም ሌላኛው ታዛቢ ሁኔታውን ሲገልጹ፣
"...እሳቱ ከተቀጣጠለ 5 ደቂቃ ብሗላ ወደ እሳት ኣደጋ ማጥፍያ ብርጌድ የተደወለ ቢሆንም በቦታው የተግኙት ግን ከኣንድ ሰዓት ንሗላ መሆኑ ታውቋል።" ብለዋል።
ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁኔታው እጅግ አስቆጥቷቸዋል እንዲህ ይላሉ፣
"ምንም አይነት ማስተባቢያ አያስፈልግም ከታሪክ ጋር ፀብ ያለው ወያኔ ታሪካዊውን ጣይቱ ሆቴልን አንድዶታል! በቅርቡ እዚሁ ሆቴል አቅራቢያ ለልማት ይነሱ የተባሉ ቤቶት በእሳት አጋይቶ ሲያነሳቸው አይተናል አሁንም የ 5 ደቂቃ ርቀት እንኩዋን የሌለው እሳት አደጋ እሳቱ እንደተነሳ ሲደወልለት እሳቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ይህን ታሪካዊ ሆቴል ካወደመው በዋላ በቦታው ተገኝተዋል ታዲያ ይሄ የማን ስራ ነው? ነው ወይስ ወያኔ ለታሪክ እሚራራ ቡቡ ልብ አለው እያላችሁን ነው?
ከታሪክ እና ከህዝብ ጋር የተጣላ ገዢ ለእያንዳንዷ ጥፋት ተጠያቂ ነው ጣቶች ሁሉ ወደሱ ይቀሰራሉ!!"
የአዲስ አበባ እና የሌሎችም ትልልቅ ከተሞች ነዋሪዎች በታሪካዊ የገበያ ስፍራዎችና በሌሎችም ታሪካዊ ቅርስነት ባላቸው ቤቶች እና ንብረት ላይ ለሚደርሱት የእሳት ቃጠሎዎች የመንግስት እጅ ሊኖርበት እንደሚችል ጥርጣሪያቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።


Saturday, January 10, 2015

ትንሽ ምስክርነት ስለ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) (ቶፋ ቆሪቾ)


merera gudina j

ከመሰንበቻዉ መረራ ጉዲና ከ25 ዓመታት በላይ ካስተማረበት ዩኒቨርሲቲ ተባረረ የሚለዉ አስገራሚና አስደንጋጭ ወሬ ከተዛመተ በኋላ አነጋጋሪነቱ ሞቅ ብሏል፡፡ (በጨዋታችን ላይ የማከብረዉ መምህሬ ስለሆነ አንተ እያልኩ ነዉ የምጠራዉ … እሱም ቢሆን አንቱታዉን ብዙም የሚፈለገዉ አይደለም … አዉቃለሁ)፡፡ በይፋ ከዩኒቨርሲቲዉ መሰናበቱን የሚያስረዳ ደብዳቤ እንደረሰዉ ባይገልጥም ነገሩ እሳት ካየዉ … ነዉ እና የምናዝን እናዝናለን፡፡
ዶ/ር መረራን ሳዉቀዉ
ለመጀመሪያ ጊዜ መረራ የሚባል ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ … በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ጎልቶ መዉጣት የጀመረዉ ይመስለኛል በ1992 ብሔራዊ ምርጫ ወቅት ነዉ፡፡ በዚያን ጊዜ የደመቀ ባይሆንም ጥቂት ፖለቲከኞች ገዢዉን ፓርቲ ሲሞገቱ የሚያሳይ የቅድመ ምርጫ ክርክር በቴሌቪዥን ይለቀለቅ ነበር፡፡ ያኔ ታድያ የብዙዎችን ቀልብ የሳበዉ በእኩልነት የምንኖርባትን አዲሲቱን ኢትዮጵያን በጋራ እንመስርት የሚል ጎልቶ የሚሰማ የአንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሑር ድምፅ ነበር፡፡ … ለእኩልነት፣ ለጋራ መብት መከበር፣ ለመቻቻል፣ ለጋራ ብልፅግና፣ ለሰላም፣ ለመጪዉ ትዉልድ አስበን በጋራ እንስራ የሚለዉ ጥሪዉን ሲያስተላልፍ ይታወሰኛል፡፡ በተለይ ሰማያዊ ቀለም ያለዉ ሙሉ ጅንስ አለባበሱን አረሳዉም፡፡ በጋራ እንስራና እንተባበር በሚለዉ የዘወትር ጥሪዎቹ ይህ ፖለቲከኛ አሁንም በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ በጉልህ ታሪኩን መፃፍ ቀጥሏል፡፡
በቴሌቪዥን መስኮት የማዉቀዉን ሰዉ ለመጀመርያ ጊዜ በአካል ያገኘሁት 1995 የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ለመቀጠል በፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሬሌሽንስ ዲፓርትመንት በገባሁበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ ፖለቲካል ገቨርናንስ የሚል የትምህርት ያስተምረን ነበር፡፡ አስታዉሳለሁ በርካቶቻችን ክፈለ-ጊዜዉን በናፍቆትና በጉጉት እንከታተል እንደነበር፡፡ ዶ/ር መረራ በሌሎች መድረኮች ላይ እንደሚያሳየዉ ተጨዋችነትና አዝናኝነት በክፍል ዉስጥም ኮሚክ ነገሮችን ይናገራል፡፡ በዚህ ዘዴዉ ትምህርቶቹን ተወዳጅ ከማደረጉም በላይ በቀላሉ ለመረዳትና ከነባራዊ ሁነቶች ጋር ለማገናዘብ እንዲቻል አድርጎ የማስተማር ብቃት እዳለዉ ብዙዎቻችን እንመሰክርለታለን፡፡ ከሁሉ የማረሳዉ በየንግግሮቹ መጨረሻ ላይ “Generally” የሚለዉን ሲሆን ሁሉ ነገር ጀነራሊ ከሆነ እንዴት ነዉ ነገሩ ብለን ብንጠይቀዉ እየሳቀ ልምድ እንደሆነበትና እየሳቀ አባባሉን ከቁም ነገር እንዳይወሰድ ያሳስበን ነበር፡፡
ዶ/ር መረራን በክፍል ዉስጥና ከክፍል ዉጪ ስናዉቀዉ የተለየ ሰዉ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር በክፍል ዉስጥ ሲያስተመር ፍፁም ሊባል በሚችል ሁናቴ ሚዛናዊና ገለልተኛ አቛሞችን ነዉ የሚያንፀባርቀዉ፡፡ የፖለቲካ እምነቱን እና አመለካከቱን በግድ ልጋታችሁ የሚል ስብእና እንደሌለዉ ወዳጆቹ ብቻ ሳንሆን ኢህዴጋዊ አቛማቸዉን በይፋ የገለጡ ተማሪ ጓደኞቻችን ጭምር ነበሩ የሚመሰክሩለት፡፡ የሚገርመዉ በ1997 የምርጫ ዋዜማ እንኳን ነገሮች ተሟሙቀዉ በተለይ ዶ/ር መረራ ሕብረት የሚባለዉን ጥምር ፓርቲ እየመራ ከቅንጅት ጋር ኢሕዴግን እንደዚያ ሲያንጰረጵረዉ፤ ዉጪ ባለዉ አቋሙ እያወቅነዉ ክፍል ዉስጥ በጉዳዩ ላይ አሰተያየት ለመስጠት እኳንን አለመፈለጉ (ብዙዎቻችን ወቅታዊ ፖለቲካዉን የተመለከቱ ጥያቄዎች እናነሳለት ነበር) የቱን ያህል ሞያዉን የሚያከበርና በአካዳሚክ ነፃነት የሚያምን መሆኑን ለማሳየቱ እንመሰክር ነበር፡፡
ከ1997 ምርጫ ግርግር በኋላ ለድህረ ምረቃ ትምህርት ተመልሼ ሳገኘዉም በቅንነት ከማስተማር በቀር በክፍል ዉስጥ ፓርቲያዊ የሆኑ ነገሮችን ላለማንሳት ሲጠነቀቅ አዉቀዋለሁ፡፡ ዶ/ር መረራ ቢሮዉ ለሁሉም ተማሪዎች ከፍት የሆነ ሲሆን ማንኛዉንም ጉዳይ ይዞ ሄዶ ምክር ለመጠየቅ የሚመችና ቤተሰባዊ መንፍስ ያለዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ከሌሎች የዲፓርትመንቱ መምህራን በተለየ መልኩ ቢሮ ዉስጥ ሲቀመጥ በሩን አይዘጋም፡፡ ስለሆነም ማንም ሰዉ ቢሄድ በቀላሉ ሊያገኘዉና ሊያወየዉ እንደሚችል አዉቃለሁ፡፡ በአጠቃለይ እንደ አብዛኞቹ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን ፊዉዳላዊ አመለካከት የሌለዉ ሰዉን በመተባበር የሚያምን ሰዉ ነዉ፡፡
ከእዉቀት አንፃር ካየነዉ በፍጹም የሚታማም አይደለም፡፡ ከብዙዎቹ የላቀ ሁለገብ የሆነ ችሎታና እወቀት ያለዉ ሰዉ ነዉ፡፡ ሲያስተምር፣ የጥናት ፁፎችን ሲያማክር፣ ሞያዊ አስተያየቶችን ሲሰጥ፣ እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ንግግር ሲያደርግ አፍ የሚያሰከፍት አይነት ነዉ፡፡ የትምህርት ክፍሉ አሉት ከሚባሉ የጠለቀ እዉቀትና የማስተማር ችሎታ ካለቸዉ የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉ መምሀራን ግንባር ቀደሙ ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ማን ይጎዳል?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በብዙ መለኪያዎች ከነበረዉ ዝና፣ ክብርና ማእረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ መምታት ብቻ ሳይሆን እየዘቀጠ እደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ጉዳይ የሚታየዉ ከአጠቃለዩ ሃገራዊ የትምህርት ጥራት መጓደልና የደረጃ ማሽቆልቆል ጋር ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የዩኒቨርሲቲዉ ዛሬ ባለበት ደረጃ ላይ መገኘት እንደ አንድ ቀደምት ሃገራዊ ተቋም መፈራረስና ሁለነተናዊ ዉድቀት ነዉ፡፡ ያን የመሰለ ታሪካዊና በርካታ ምሁራንን ለሃገሪቱ ያፈራ ተቋም ዛሬ ላይ በአለም ከፍተኛ ዝና ካላቸዉ የትመህርት ተቋማት ጋር መወዳደር ሲገባዉ በአፍሪካ ዉስጥ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል ቦታ የለዉም፡፡ ይኼ ጉዳይ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ ላለፍን ሁሉ አንግት የሚስደፋ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለምን ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ብራንድ አይኖራትም ብለን ለምንጠይቅ ምላሹ ምን ይሆን?
ከዩኒቨርሲቲዉ ዝቅ ብለን የፖለቲካ ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሬለሺንስ (PSIR) የሚባለዉን የትምህርት ክፍል ያየን እንደሆነ የበለጠ የሚስደነግጥ ማሽቆልቆል ሂደት ዉስጥ እንዳለ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በርካታ እጋፋና ወጣት መምህራኖች በየጊዜዉ እየለቀቁ በመዉጣታቸዉ የትምህርት ክፍሉ በህንድ መምህራን እና አንዳንድ ነዉረኛ ሰዎች እንዲሞላ ተድረጓል፡፡ እዚህ ላይ የማስታዉሰዉ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወቅቱ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዘዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ዘመድ እንደሆነ በፉከራ ይናገር የነበር ዶ/ር ኤርሚያስ አበበ (ያባቱን ስም ካሳትኩ ይቅርታ) የሚባል ሰዉ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን ‘Foreign Policy and Diplomacy’ የሚል የትምህርት አይነት እንዲያስተምር ተመድቦ በርካታ የሚያሳፍሩ ተግባሮችን ሲፈፅም እንደነበር ምስክርነት ለመስጠት እችላለሁ፡፡ በስካር ጥንብዝ ብሎ በወሳንሳ በመጠጥ ቤት ጓደኞቹ ተደግፎ ከመምጣቱ በተጨማሪ በነዉረኛ ስድቦች ተማሪዎችን ይዘለፍ ነበር፡፡ የትምህርት ክፍሉ አሉት የሚባሉ ማምህራን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ እንኳን ፍልሰት በሚመስል መልኩ በመልቀቃቸዉ የቱን ያህል የተዳከመ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡
እናም የዶ/ር መረራና መሰል አንጋፋና ጠንካራ አመለካከት ያላቸዉ ምሁራን መልቀቅ የትምህርት ክፍሉን እና ዩኒቨርሲቲዉን ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችለዉን ኪሳራ ማስላት አዳጋች አይሆንም፡፡

Saturday, January 3, 2015

ወያኔ የጉራጌ ማህበረሰብ ከሌላው የህብረተሠብ ክፍል ለማጋጨት በወልቂጤ ዩኒቨርሥቲ እየፈጸመው ያለው ደባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው ይገባል


ከላይ በርዕሱ ላይ የጉራጌ ማህበረስብ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ብዬ የተጠቀምኩት ወያኔ/ኢህአዴግ በጉራጌ ዞን በቸሃ ወረዳ ጉብሬ ከተማ ላይ በህዝብ ድጋፍና እርብርቦሽ የተመሠረተችው ወልቂጤ ዩኒቨርሥቲ ውሥጥ በተግባር እያደረገ ያለውን ጉዳይ ነጠል አድርጌ ለማሣየት እንጂ ወያኔ በሁሉም የሐገራችን ክፍል የተሠማራበት እኩይ ተግባር ጠፍቶኝ እንዳልሆነ ልትረዱልኝ እፈልጋለሁ። ባጠቃላይ ወያኔ ኢትዮጵያ ሐገራችን ለማጥፍት ግቡ አድርጎ የሚንቀሳቀስ የትኛውንም ህዝብ ሊወክል የማይችል በጥቂት ማፍያ ወንበዴዎች የሚመራ የሆዳሞች ድርጅት ነው። የመጨረሻ የሆነውን ሐገር የማፍረሥ አላማቸው እውን እሥኪሆን ድረሥ ሀገሪቷን መምራት ስለ ሚፈልጉ ህዝቡ አንድ እንዳይሆን የተቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኻላ እንደሚያደርጉ ልንገነዘብ ይገባል።
ከፋፍለህ ግዛ (በዘር) መርህ የሚከተለው ወያኔ ላለፉት 23 ዓመታት ህዝቡን እርስ በርስ እንዳይተማመን፤ እርስ በርስ እንዲተላለቅ፤ እርስ በርስ እንዲጥላላ አያሌ ሥራዎችን ሠርቷል። ህዝቡን በዘር፣ በሐይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በእምነትና በሌሎችም ተመሣሣይ ጉዳዮች ለመከፍፈል በፖሊሲ ደረጃ ተቀርጾ ሲመሩበት የነበረና አሁንም ያለ ህዝብ ፍቃድ የገፉበት ጉዳይና ፖሊሲ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ3000 አመት በላይ ተከባብሮና ተቻችሎ፣ ያሉትን ልዩነቶች አጥብቦ የኖረባት ሐገር ዛሬ የዘር ፖለቲካን በማራመድ በህዝብ ዘንድ ጥላቻን በማሥፈንና ልዩነቶችን በማስፋት የኢትዮጵያ ህዝብ ሆድና ጀርባ ለማድረግ ተግተው እየሠሩ ነው። ወያኔ በዚህም ተግባሩ ከልማት መንገድ ይልቅ የጥፍት መንገድ መምረጡን ያመለክታል።

ወያኔ በዚህም መሠሪ ተግባሩ ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለታል ማለት ባይቻልም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ግን የዚህ ተግባር እርዝራዦች፣ አደር ባዮች፣ አጎብዳጆችና ሆዳሞች ግን አልጠፉም። አንዳንዶቻችን የወያኔ መሠሪ ተግባርና አላማ ጠንቅቀን የምናውቅ ብንሆንም ከወጥመዱ ማለፍ ያልቻልን ደካሞችም መኖራችን ግን አልቀረም። ወያኔ ሁላችንም ጠባብና ትምክተኛ እንድንሆን እንደሚፈልግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠንቅቆ የሚያውቀው ይመስለኛል። ይህ ከሆነ ደግሞ ሁላችንም ወጥመዱ ውስጥ እንዳንደናቀፍ አስፈላጊ ጥንቃቄ መውሠድ ይጠበቅብናል። ያ ሳይሆን ሲቀር ግን እራሣችን ወያኔ ባዘጋጀው መረብ ውስጥ ተጠልፈን ትክክለኛ መሥመር እየተከተሉ ያሉትን ማደናቀፋችን ወይም እየተከተሉት ላለው የለውጥ ጎዳና እንቅፍት መሆናችን አይቀሬ ነው። በዚህ ጊዜ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወያኔ መሣሪያ ሆነናል ማለት ነው።

ወደ ዋናው ጽሁፌ መለ ወያኔ በወልቂጤ ዩኒቨርሥቲ እያደረገ ያለውን ነገር አሣሣቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት ነው። ይህም ዩኒቨርሥቲው ውጥ ወያኔ የራሱን ሠዎች በማዘጋጀት ፍራሽ ከተደረደረበት ክፍል እስከ የተማሪ ማደሪያ የሆኑትን ዶርሚተሪዎችን በማቃጠል ከሌላ ክልል የመጡት ተማሪዎች ድርጊቱን እንደፈጸሙት በማድረግ የጉራጌ ማህበረሰብ ከሌላ ክልል ለመጡትን ተማሪዎችም ሆነ ስለ ሌላው ማህበረሰብ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው ለማድረግና እርስ በርስ ለማጋጨት ነው። 

በመሠረቱ የጉራጌ ማህበረሰብ በሁሉም የሐገራችን ክፍል በተለያዩ የግልና የመንግሥት መሥሪያ ቤት በተለይ የንግድ ሥራ ላይ ተሠማርቶ የሚሠራ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉም የሐገራችን ክፍል የሚመጡ ሰዎች ጋር በደንብ የመገናኘት አጋጣሚ ስላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል ጨዋ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በዚህም ምክንያት ወያኔ የሚፈጸማቸው ድርጊቴች ወይም የወያኔ ሴራዎች ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ታህሳስ 25, 2014 እ፣ኤ፣አ ጠዋት በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሁለት ተማሪዎች (አንደኛው ከአማራ ክልል የመጣ, ሁለተኛው ከኦሮምያ ክልል) መጣላታቸውን ተከትሎ ከኦሮምያ ክልል የመጡት ተማሪዎች የግቢው ህንጻዎች ላይ በሌሊት አደረሱት የተባለውን ጉዳት ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የፈጠረው መጥፎ ስሜት ነው። እዚህ ላይ ሁሉም የጉራጌ ማህበረሰብ ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር የዚህ ሁሉ ተጠያቂው ወያኔ መሆኑን ነው። ምክንያቱም የኦሮሞ ህዝብ ለብዙ አመታት ከጉራጌ ማህበረሰብ አብሮ የኖረና ተጋብቶ የተዋለደ እንደመሆኑ መጠን ምንም አይነት ችግር እንደሌለባቸው ነው። ስለዚህ የተፈጠረው ድርጊት በማንም ይሁን በማን ወያኔ ህዝቡን ለማጋጨት ሆን ብሎ የፈጸመው እንጂ ከኦሮሞ ማህበረሰብም ሆነ ተማሪዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ነው። ለወደፊትም ቢሆን ጥንቃቄ ልንወስድ ይገባል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

http://www.zehabesha.com/