Wednesday, December 4, 2013

አምባሳደሩ የግብፅን መንግስት አቋም አላብራሩም


የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አካል የሆነው የአባይ ወንዝ አቅጣጫ የማስቀየር ስራ መከናወኑንና በግብፅ በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተቋቋመው የኤክስፐርቶች ቡድንን ሪፖርት ይፋ መደረግን ተከትሎ ከግብፅ በኩል እየተሰሙ ያሉ ጉዳዮችን በሚመለከት የመንግስታቸውን አቋም እንዲያብራሩ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ የቀረበላቸው በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር እስከአሁን ማብራሪያቸውን አላቀረቡም፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ከማል አሚር፤ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመወያያት በቀጣዮቹ ቀናት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የተለያዩ ሚዲያዎች የዘገቡትና በኢትዮጵያም በኩል እንደሚመጡ መረጃው ያለ ቢሆንም፣ በተባለው መሠረት ይመጣሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ከምንጮቻችን ለመረዳት ችለናል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ጉዳይ ሰሞኑን ማብራሪያ የሰጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ዲላሚኒ ዙማ፤ ኢትዮጵያና ግብፅ ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
ግብፅ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙ ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ “ታሪካዊ መብቴ ነው” በማለት ትሟገታለች፤ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ደግሞ በ2010 የተፈራረሙትን በወንዙ ላይ የግብፅን ፈቃድ ሳይጠይቁ ለመስራት ተስማምተዋል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ጉዳዩ በአዲሱ ስምምነት እንጂ በቅኝ ገዢዎች ዘመን በተደረገው ስምምነት መታየት የለበትም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አሊ አህመድ ከርቲ፤ ሰሞኑን አዲስ አበባ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሱዳን የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት እንደተቀበለችውም አስታውቀዋል፡፡ የነጭ አባይ ምንጭ የሆነችው የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው፤ በግብፅ ላይ መረር ያለ ትችት ሰንዝረዋል፡፡
የግብፅ መሪዎች፤ የቀድሞው አመራሮችን የተጣመሙ ፖሊሲዎች መከተል እንደሌለባቸውና የግድቡ መሰራት ለሌሎች አገራት ስጋት ሊሆን እንደማይችል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም አፍሪካዊ ግብፅ እንድትጎዳ አይፈልግም፤ ይሁን እንጂ ግብፅም ጥቁር አፍሪካውያንን መጉዳቷን መቀጠል የለባትም ብለዋል – ሙሴቬኒ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳኑ ፕሬዚደንት አልበሽር፤ ለሶስት ቀን የሚቆይ ጉብኝት ለማድረግ ከትናንት በስቲያ ኤርትራ የገቡ ሲሆን የፕሬዚደንት ጉዳዮች ሚኒስትር፤ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና የፀጥታ እና የደህንነት ሚኒስትሮቻቸው አብረው መጓዛቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን የሁለቱን ሀገሮች መሪዎች በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በስልክ እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment